ዮሐንስ ሞላ's Blog, page 6
November 25, 2019
November 17, 2019
November 10, 2019
November 3, 2019
October 6, 2019
እንጉርጉሮ ለኤልያስ መልካ – Elias Melka
ለኢትዮጵያ የሙዚቃ ኢንዱስትሪ በዜማ፣ በግጥም እና በቅንብር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደረገው ውዱ ኤልያስ መልካ የሰላም እረፍት ይኾንለት ዘንድ እንመኛለን። ፈጣሪ ነፍሱን በቀኙ ያሳርፋት። ለቤተሰብ፣ ለሙያ አጋሮቹ እና ወዳጆቹ መጽናናትን እንመኛለን። እጅግ በላቁ ስራዎቹ ዘወትር እንደተወደደ እና፣ በክብር በልባችን እንደተዘከረ ይኖራል። ስለዚህም፥ አረፈ እንጂ ሞተ አንልም።
October 1, 2019
“ጎዳናው እስኪቋጭ” የአሳዬ ደርቤ አዲስ መጽሐፍ
[image error]ሽግግሩ ከተከሰተበት ጊዜ አንስቶ በየቀኑ የሚሰሙ ቅስም ሰባሪ ሰበር-ዜናዎች ከመብዛታቸው የተነሳ ለማስታወስ ያዳግታል፡፡ እመርታዎቹ ደግሞ የማይታዩና የማይጨበጡ በመሆናቸው ማይክሮስኮፕ ላይ ተጥዶ ምርምርና ጥናት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡
ከለውጡ ወዲህ የተቀጠፉት ነፍሶች ይሄን ለውጥ ለማምጣት ከተሰውት እየበለጠ ነው፡፡ ይሄም ሆኖ ግን ሰውዬው በምታለቅስ አገር ላይ ፈገግ እንዳለ ቀርቷል፡፡ ሁሉም ነገር የሚሆነው በእሱ ይሁንታ ይመስል፣ በተደናገረው ሕዝብ መሀከል በሁለት ዙር ግንብ ካሳጠረው ቤተ-መንግሥቱ ውስጥ ሆኖ በቃላት ይፈላሰፋል፡፡
*
የመጻፍ ሙዳችን እየመጣ ነው፡፡
ስለምን እንጻፍ? ስለምን እንፈላሰፍ?
“ሽግግር- ከችግር ወደ ችግር” የሚል ርዕስ አስምረን ችግሮቻችንን እንዘርዝር?
ነው ወይስ…
“ለውጥ- ከማጥ ወደ ማጥ” የሚል አጀንዳ ይዘን “እንደ አገር” አብረን እንስመጥ?
ድል- ከትግል ወደ ትግል
ድልድይ- ከገደል ወደ ገደል
ምናምን፣ ምናምን እንበል?
ወይስ?
ለውጡ እንዳይቀለበስ
ትችታችን ጋብ አርገን- ንፋሱን ጋልበን እንንፈስ?
*
እኛን ያላዩ ፈረንጆች-በእውቀት፣ በሀብቱ የታደሉ “A problem well-stated is a problem half solved” ይላሉ፤ “ሙሉ በሙሉ የታወቀ ችግር በከፊል ምላሽ አግኝቷል” እንደ ማለት፤ ታዲያ የኛ ደዌ እና ተውሳክ- ሙሉ በሙሉ ታውቆ ሳል- እንዴት መፍትሄ ታጣለት? ለዶክተሩ የነገርነው በሽታችን ሊድን ቀርቶ ስለምን ነው የባሰባት? መልሱ ቀላል ነው! በሽታችን ገሃድ ወጥቶ-እንደ ብቅል- ከጸሐይ ላይ ቢነጠፍም መርፌና ሐኪም ከለገመ- እንኳን ታፋ- ቅቤ አይወጋም፡፡ በሺህ ቃላት ቢቀባቡት- የመርዝ ውህድ- ሽሮፕ ሆኖ አይፈውስም፡፡ በመሆኑም… ዶክተር በምድሩ ሳለ- ቅስቻችንን ያበረታው- የተያዝነው በጣር፣ ሲቃ “ሕመማችን ታውቆ ሳለ- መዳኒቱን ተነፍገን ነው” ብዬ ላብቃ፡፡
መሸጫው፡ $19.99
(መላኪያውን ጨምሮ | shipping included)
ለመግዛት ከታች ይጫኑ
September 29, 2019
ጉራጌ እና ማህበራዊ ትውፊቶቹ (በጥቂቱ)
በነገራችን ላይ፥ ጉራጌ ካለው ነገር አንዱ፣ ምናልባትም በደንብ ያልተነገረለት፣ የመስጠት ባህሉ ነው። የምርቃት ባህሉም ሌላው ነው። ግፍ፣ ነውር ይፈራል። ቀመጥ ይሰርፍ ይባላል።
እንደ ጥሩ ምሳሌ፥ በመውደድ ክብሩ “ያዊዌ” ዘፈን ላይ፣ ሽምግልና ተልኮ ልጅቷ ትሰጠው ወይ?” ተብሎ መጠያየቃቸው፣ እሱም እሷን አይቷት ልቡን ከጣለ በኋላ መጨናነቁ፣ በኋላም ሲሳካለት ሰዉን በግብዣ ሲያንበሸብሽ ነው ታሪኩ ማጠንጠኛው። (“ያዊዌ” ማለት “ይሰጠው ወይ?” ማለት ነው።)
ተፈቃሪዋ ቆንጆም፣ ለትዳር የሚሆናት የማይሆናት መሆኑን ለማወቅ ሶስት ጥያቄዎች ነው የምትጠይቀው
1) ንቅ ቃር ትረምዴ ዌ? (በጣም ትወደኛለህ ወይ?)
2) ሜና ትረምድ ዌ? (ሥራ ትወዳለህ ይ?)
3) ቀመጥ በሰረፍከ (ነውር፣ ግፍ ከፈራህ) …መውደድ እናቴርኸ (አታርፍድ ውሰደኝ) ነው የምትለው።
እንጂ እንደተለመደው “ቤት አለው ወይ? ስራው ምንድን ነው? ንብረቱ ምንድን ነው?” የሚሉ ባህላዊ የሽምግልና ጥያቄዎች አይደለም የሚነሱት። ግፍ ከፈራ፣ ከወደዳትና ሥራ ከወደደ በቂዋ ነው። ሁሉንም ሰርተው እንደሚያገኙ ታውቃለች።
በልምድ ገኖ የሚወራው ቋጣሪነቱ፣ ከምክንያታዊነት ጋር የሚያያዝ ነው። እንጂ ስስት አያውቅም። በነገራችን ላይ ጉራጌን ቋጣሪ የሚሉት፣ የሰው ንብረት የሚመኙ ወይም ቁጭ ብለው መቀለብ የሚፈልጉ ናቸው። ለሰው በሙሉ እጁ ቁም ነገር የሚሰራበትን ይሰጣል እንጂ፣ እንዲመላለስ የሚያደርግ ቁጥ ቁጥ አያውቅም። ሰው በልቶ የሚጠግብም አይመስለውም። የገንዘብን ጥቅም እና አመጣጡን ያውቃልና ካላግባብ የሚወጡ ብሮች ያናንዱታል።
ጋብዞ፣ ድግስ ጥሎ፣ ወይ ሰው ለመርዳት በአግባቡ የሚያወጣው 100 ሺህ ብር እና እንዲሁ ተሸውዶ ወይም ያላግባብ የሚያወጣው 100 ብር ስሜት ሲነጻጸሩ፣ የ100 ብሩ ያበግነዋል። አዲስ ሰው ወይም የከሰረ ወዳጁን ስራ ለማስጀመር ያለውን ከማዋጣት አንስቶ፣ እቁብ ሰብስቦ አንደኛ እጣ በመስጠት ባህሉ ይታወቃል። በሀዘን እና በደስታም አብሮ ተካፋይ ነው እንጂ የዳር ተመልካች አይደለም።
በአካባቢ በጎ ፈቃደኝነት ስራም (voluntarism) ጉራጌ ስመ ጥሩ ነው። በየደረሰበት አካባቢውን ምቹ ለማድረግ ይተጋል። ሁሉም ጋር ይዞራልና ሁሉም ቤቱ፣ ሁሉም አገሩ ነው። መንግስት ሳይቀሰቅሰው ኮሚቴ አዋቅሮ፣ በሰንበት አካባቢውን ያያል። ጉብታውን ሜዳ ያደርጋል። ገደሉን ይሞላል።
ሌላው ደግሞ የሴቶችን ነጻነት/እኩልነት ለማስከበር ያለው ታሪኩ ተጠቃሽ ነው። ዓለም ፌሚኒዝምን ማቀንቀን ሳይጀምር “እምቢ አሻፈረኝ” ብላ አምጻ፣ ሴቶቹን አሳምጻ መብት ያስከብችው ፌሚኒስት ጉራጌዋ የቃቄ ውርድወት ናት። ታሪኩ በቴአትርም ተሰርቶ ብሔራዊ ቴአትር ታይቷል። እንዲሁም የእንዳለ ጌታ ከበደን “እምቢታ” ብታነቡ ትደነቃላችሁ።
ከዚህም ባሻገር በበዓላት የወንዶች እና የሴቶች የስራ ክፍፍል አለ። ሶፋ ላይ ተጋድሞ ሪሞት እየነካኩ “አልደረሰም” ወይ የማለት ቅንጦት የለውም የጉራጌ ወንድ። ተፍ ተፍ ብሎ፣ እንጨት ፈልጦ፣ ኮባ ቆርጦ፣ ደጅ አጽድቶ አብሮ በስራ ይሳተፋል። በከተፋ ጊዜም ስጋ በመመራረጥ እና በመለየት ያግዛል። የሚከትፍም አጋጥሞኝ ያውቃል።
ከመስቀል በዓል አንድ ቀን ቀድሞ ያለው ቀን፣ ዴንጌሳት ወይም የሴቶች መስቀል ነው የሚባለው። የሴቶች መስቀል መባሉ፣ ሴቶች ሙሉ ለሙሉ ከወጪ እስከስራ ራሳቸው ችለው የደረሰውን እንግዳ ስለሚያበሉ ነው። ተራ ቢመስልም፣ እንደእኛ ብዙ በሚቀረው እና ሴት በደመወዝ ስትበልጠው በሚከፋ ማህበረሰብ ውስጥ፣ አንድምታው ትልቅ ነው።
እንደዚሁም አስተርዮ ማርያም የሴቶች ገና በመባል ይታወቃል። እንደፈለጉ አምሽተው፣ አድረው ሲጫወቱ እና ሲበሉ ቢያነጉ ማንም አይታዘባቸውም፣ አይናገራቸውም። አሁን አሁን ዘመን ሲሰለጥን ቀረ እንጂ፣ የፊቂይር ገብያ በሚባል የሚታወቅ የመተጫጨት የጨዋታ ስርዓት ነበር። እዚያ ላይ ወንዱ ብቻ አይደለም የመምረጥ መብት የነበረው። ሴቷም ልቧ የፈቀደውን በዘፈን ግጥም እየደረደረች፣ ወይም በዐይን እየተያየች ስሜቷን ታስተናግዳለች። ለዚያም ነው ገበያ መባሉ። ሸጪ እና ገዥ ካልተስማማ ነጥቆ መሮጥ የለ ገበያ ውስጥ።
በዓል በመጣ ጊዜም፥ ለቤቱ ሰንጋ ሲጥል አካባቢው ላይ ያጡ፣ ባል/ወላጅ የሞተባቸውን እና አረጋውያን ጋር ስጋ ይልካል። ወይ ደግሞ ይገዛላቸዋል። በዚህም ምርቃት እና በረከት ያገኛል። ለመመረቅ በጣም ነው የሚለፋው። ከከተማም በአቅም ማጣት መሄድ ያልቻሉ ሰዎችን እቃ ገዝቶ፣ ከራሱ ጋር አሳፍሮ ይዟቸው ይገባል እንጂ ብቻ መብላት ብሎ አይታሰብም።
ጉራጌ ወዳጅ፣ ጎረቤት ያላችሁ መስክሩ።
ብቻ በወዳጅ ቆስቋሽነት፥ don’t mess up with Gurage people ለማለት ያህል ነው! ሃሃሃ…
“ስለ ትናንሽ አለላዎች” የዮናስ አ. መጽሐፍ
[image error]ወጣትነት እንደቢራቢሮ ተራራ የተከመረ ቀለም ነው። ብዙ መልክ ያለው ግን በቀላል ንፋስ እንደአመዳይ የሚበተን። ምናልባት ማሰብ ከሚገባን በላይ እናስባለን። ወይም በተቃራኒው።
*
ጠይም ባቶች የፈጠረ ማነው? እግዚአብሔር አይደለምን? ቆንጆ አድርጎ የሚፈጥር ማነው? ጦሳ አይደለም ወይ? የሚያነሳ ማነው? የሚጥልስ? የሚያድን ማነው? የሚገድልስ? …
ሞት ሲመጣ እንዴት ነው? እንደነፋስ? እንደ ደመና፣ እንደ ጭጋግ መሰስ ብሎ? እንደ እንግዳ ድንገት ከተፍ? እንደሽታ፣ እንደሰንደል ጢስ? እንደምሽት፣እንደ ጨለማ?
*
አንድ ቀን ግን በቀትር ብቻቸውን ተቀምጠው ሲያንጎላጁ ሳለ፥ መጣ። ተጠርቶ የሚመጣ ሞት የለም። ዐይኖቻቸውን ሲከፍቱ ነጭ ሸማውን አጣፍቶ ለብሶ ፊት ለፊታቸው ተገትሯል። ከቤታቸው ውስጥ የሰንደል ጢስ ጉበኑን እየላሰ ወደ ውጭ ይተናል።
“ውይ ሞትዬ፥ መጣህልኝ?”
“መጣኹኝ።” እየፈገገ፣ እየተሽኮረመመ፣ ደግሞ እየተንጎማለለ።
“በል ልብሴን ልልበስ፣ ልተጣጠብ ጠብቀኝ።” አሉት።
እየሣቀ ቀረባቸው…
*
“…ምናልባትም ፀሓያማ የመስከረም ከሰዓቶቻችንና በጠራ የታህሳስ ሰማይ በምሽት ያየናቸው ወርቃማ አብረቅራቂ ከዋክብት በትናንሽ ሓልዮቶቻችን ውስጥ የተከሰቱ ትላልቅ ተዓምራቶች ሊሆኑ ይችላሉ። አማልክት ነንና።
ምናልባት ሕይወታችንን ሙሉ የምንባክነው ያሳለፍነውን መልካም ነገር ፍለጋ ይሆናል። መዋቲ ነንና። ደግሞም ስግብግቦች። ህይወት ክብ ናት የሚሉ አሉ።
ምናልባት ይሄ ኹሉ ነገር፣ የኾነውና ያልኾነው፣ ገና የሚኾነውም ኹሉ በሙሉ አእምሯችን ውስጥ የተጋነነ የቀን ሕልም ነው።
ወይም ደግሞ ምናልባት ኹሉም እንደምናየው እንደምንሰማው መጠን እውነት ነው።
ምናልባት . . .”
—————————————————–
መሸጫ፡
September 25, 2019
የቀጠለ… (ከዴቪድ ጋር)
“አይ እሱን እንኳን ነገሩን ቀድሜ ስለማውቀው ብዙም አያጣላንም። ማወቅ ረጋ እንድትል ይረዳል። ስለምረዳት አልፋታለሁ።”
“ታዲያ ምንድን ነው? የሚነገር ዓይነት ከሆነ ነው የምልህ… ካልሆነም አትጨነቅ”
“ችግር የለውም። እነግርሃለሁ። ዋናው ነገር እኔም እሷም ትንሽ እረፍት ፈልገናል መሰለኝ። አንዳንድ ጊዜ በአንዱ መኖር የሚሸፈንልህን ነገር፣ ያ ሰው ጎድሎ ካላየኸው አታመሰግንም። ሁሉንም ነገር እንደ ተራ ጉዳይ ትቆጥረዋለህ። እሷም እኔም ዋጋችንን እርስበርስ እንድንተዋወቅ ይጠቅመናል። በዋናነት የግጭት መንስኤ የነበረው፣ ተራ ነገር ነው። ምን መሰለህ፥ ያዋጣናል ብለን የሆኑ እቃዎችን ሸጠን ነበር። ሀላፊነቱ ለእኔ ነበር የተወሰነው። ልክ እኔ ከሸጥኩት በኋላ ዋጋው ተወደደ።
መጀመሪያ ሳማክራት በስራ ስለምትጠመድ አንተ እንደፈለግኽ አድርግ ብላኝ ራሷን ገለል አድርጋ ነበር። እኔ ደግሞ የራሴን ጥናት አድርጌ፣ ሰዎች አማክሬ ሸጥኩት። በኋላ የተሻለ ዋጋ ማውጣት የሚችል ነገር መሆኑ ተገለጠልን። እና ጭቅጭቅ ጀመረ።
“ሳማክረሽ ችላ ብለሽው። ልብሽ ሁሉ ስራሽ ላይ ነው ያለው።” እላታለሁ፤ “አንተ ነገሮችን እንደፈለግኽ ነው የምታደርገው፣ ግድ የለህም” ትለኛለች።
ነገሩ ምክንያት ነው የሆነን እንጂ ጊዜ የሚጠብቅ ነገር ነበር። ያንን አጋጣሚ ተጠቅማ እሷ ከእኔ የተሻለ አሳቢ እና አዋቂ መሆኗን ለማሳየት ትፈልጋለች። እኔም አጋጣሚውን ተጠቅሜ፣ ልቧ ስራ ላይ ብቻ መሆኑን በማስታወስ የእኔን በደል እዘረዝራለሁ።
ታውቃለህ፥ በስራ በጣም ስለምትጠመድ ብዙ ነገሮች ያልፏታል። ደግሞ የቤተሰብ ሀላፊነቱ፣ እናትነቱ ስላለ አያስችላትም። ቤት መሆን መሳተፍ ትፈልጋለች። ታሳዝናለች።” አለኝ ሀዘኔታ እና ግራ መጋባት የተደባለቀበት ፊት እያሳየኝ
“ስራዋ ምንድን ነው?”
“ሀኪም ናት። ኦንኮሎጂስት ናት። ከባድ ሀላፊነት አለባት። ህክምና ስራውም ይበዛል፣ እሱ ላይ ደግሞ፥ እሷ በጣም ስራ ወዳድ ናት። አሁን እኔና አንተ እያወራን ብደውልላት እንኳን ኮምፒዩተሯ ላይ ተጥዳ የታካሚዎቿን መረጃዎች ስታስተካክል፣ ወይ የነገ ኬዞችን ስታደራጅ ነው የምታመሸው። እኔ ሁሌም ልረዳት ነው የምሞክረው። በስራዋ ደስተኛ ነኝ። ህክምናውን ባውቅና፣ ብችል ባግዛትም ደስ ይለኝ ነበር። ግን ደግሞ የስራ እና የኑሮን ጉዳይ ሚዛን መጠበቅ አለብህ።”
“እውነት ነው”
“ቀላል ምሳሌ ልንገርህ። ብዙ ጊዜ የሚከሰት ነው። ከምሽቱ 12 ሰዓት አካባቢ ቴክስት ተደራርገን ወይ ተደዋውለን እየመጣሁ ነው። ትለኛለች። እኔም እሺ ብዬ ምትበላውን አዘጋጅቼ፣ ምትጠጣውን አዘጋጅቼ እጠብቃታለሁ። 1 ሰዓት፣ ወይ 2 ሰዓት ያልፋል። በመሀል መሄድ የምፈልግበት ቦታ ካለ ወይ ወዳጆቼ ከጠሩኝ የጽሁፍ መልዕክት ትቼላት እወጣለሁ። ታብዳለች። እሷን ለማናደድ ያደረግኩት ያህል ይሰማታል። እሷ ጉዳይ ካለባት ሌላ ሰው ጉዳይ የሌለበት ይመስላታል። ራሷን ብቻ ነው የምታዳምጠው። ብዙ ነገሮች እሷ ስታደርጋቸው ልክ ሆነው ይኖሩና፣ ልክ እኔ ሳደርጋቸው ስህተት ይሆናሉ።” ብሎኝ ሳቀ። በፈገግታ አጀብኹት።
“እህ…” አልኩኝ የምሰጠው አስተያየት ነገር ያግል፣ ነገር ያብርድ ስላልገባኝ፤ ጨዋታው እንዲቀጥል በመፈለግ፥
“ሌላ ምሳሌ ልስጥህ፥ ከልጆቼ ጋር ባለኝ ግንኙነት ትቀናለች። ቅድም ተደዋውለን ራሱ አንድ ሁለት ተባብለናል። ልጃችን ከኒውዮርክ ነገ ትመጣለች። ቀድመን ሁለታችንም እናውቃለን። ነገር ግን ከአውሮፕላን ማረፊያም እንድቀበላት ስለምትፈልግ ዛሬ እኔ ጋ ደወለችልኝ። ቅድም ስደውል መደወሏን ነገርኳት።
“ለምንድን ነው እኔ ጋር ያልደወለችው?” አለችኝ። ለምን ልበላት?
እኔ የስራ ፀባዬም ጊዜ ስለሚሰጠኝ፣ በተፈጥሮዬም እንደዚያ ስለሆንኩ ልጆቼ ጋር በየቀኑ አንድ ደቂቃም ቢሆን እደውላለሁ፤ ያንን ለምደው ሳልደውል ስቀር ደግሞ እነሱም ይደውላሉ። እሷም ጋር ይደዋወላሉ። ግን ያለባትን ጫና ስለሚያውቁ፣ ብዙምም ፊት ስለማትሰጣቸው አጥሯን ያከብሩላታል።
እኔ አብሬያቸው መሬት ላይ ስንከባለል፣ ትራስ ስወራወር፣ ስላፋ፣ ቴኒስ ስጫወት ነው ማሳልፈው። እሷ ያንን ለማግኘት እድሉም የላትም። ከስራ ጸባዩዋ አንጻር ይህንን ማድረግ ለእሷ ቅንጦት ነው። በዚህም የተነሳ ልጆቻችን እኔን የበለጠ ይቀርቡኛል። የምልህ እሷንም ይቀርቧታል፣ ግን እኔ ጋር ይበልጥ ይሆናሉ። እሷን ይረዷታል። ዝም ብለው ሄደው አይረብሿትም። ነይ እንውጣ፣ ገበያ እንሂድ፣ ሜዳ እንሂድ አይሏትም። ትልልቆች ስለሆኑ ያውቃሉ።
እሷ ለመታቀፍ እና ለመሳም “እኔስ” ብላ ጠይቃ ነው እንጂ ዝም ብለው ሄደው አይጠመጠሙባትም። እሷም ያን ያህል ጊዜ መስጠት ብትፈልግም አትችልም። ስራዋ በጣም ይፈልጋታል። የብዙ ሰዎች ሕይወት እጇ ላይ አለ። እና ከእኛ ጋር መሆኑ ቅንጦት የሚሆንበት ጊዜ ብዙ ነው።
ሀኪም ማግባት ቀላል ነገር አይደለም። በጣም ከባድ ነገር ነው። ሀኪም ካላገባህ ወይ ሀኪም ካልሆንክ አይገባህም። ከሀኪም ጋር ጓደኝነት እንኳን ከባድ ነው።
በብዙ ውጣ ውረድ ነው የምታልፈው እሷ። የተለያዩ ታካሚዎች ይመጣሉ። የተለያዩ ታሪኮችን ትሰማለች። በመሀል ቆዳዋ ጠንክሯል። ሞት አይደንቃትም። የምልህ፥ በግዷ ትጠነክራለች። ጠንካራ ተመስላለች። ብዙ ጊዜ ሰው ሲሞት አይታለች።
የረዳችው ሰው፣ ለክፉ አይሰጥህም ያለችው ሰው፣ ተስፋ የሰጠችው ሰው፣ የተላመደችው ሰው ሲሞት አይታለች። ለቤተሰብ ዓይናቸውን እያየች የሟቹን ወሬ ማርዳት አለባት። ስራዋ ያስገድዳታልና አብራም ማልቀስ አትችልም። ዓይናቸውን እያየች፣ ፊትለፊታቸው ቆማ “ስነግርህ አዝናለሁ። ሚስትህ ሞታለች” ትላለች። ቀላል አይደለም። በሀዘኑ ብዛት ድብርት ውስጥ ገብተው መልሰው እሷ ጋር ይመጣሉ። መርዳት፣ ሪፈር መጻፍ አለባት። ነገ ያንን ወሬ ከአንዱ ለማስቀረት ስትል ዛሬ ብዙ መስራት እንዳለባት ታስባለች። ቀላል አይደለም። እና አንዳንዴ ትንሽ የራሷን ቦታ ልትፈልግ ትችላለች። በአንድ መልኩ እሷንም እኔንም ለመርዳት ነው ለጊዜው ገለል ማለት እንዳለብኝ የወሰንነው።”
“አይዞን! (የአይዞንን ትርጉም አስረድቼው ቃሉን እሱም ይጠቀማታል) ሁሉም ጥሩ ይሆናል። በቅርቡ ሁሉም ተስተካክሎ አብራችሁ እንደምትሆኑ ተስፋ አደርጋለሁ።” አልኩት።
“ይመስለኛል! በቀጣዩ ወር የጋብቻ አማካሪ (marriage counselor) ጋር ለመሄድ ቀጠሮ ይዘናል። ነገሮች ጥሩ መሆናቸው አይቀርም።”
መልካም ምኞቴን ተመኝቼለት ሌላ ጨዋታ ቀጠልን።
September 7, 2019
“ሴቶች አስቂኝ ናቸው”
ከዴቪድ ጋር ለጥቂት አፍታ ዝም ተባብለን ስለሚስቱ ጠየቅኹት።
“ታውቃለህ ዮሐንስ፥ ሴቶች በጣም የሚያስቁ ፍጥረቶች ናቸው” ቀጥሎ ያለውን ለመስማት በመጓጓትም፣ በደምሳሳው የደመደመው እንደው ለመከላከል በመሻትም
“እንዴት?”
“ናቸዋ!”
“ቀላል ነው? እንዲህ ብለን ማጠቃለል እንችላለን ዴቪድ?”
“ታውቃለህ? በጣም ነው የሚያስቁት። አስቂኝ ፍጥረቶች ናቸው። የዛሬ 20 ወይ 25 ዓመት ያደረግኸውን ነገር በፈለጉት ጊዜ ያስታውሱታል። ከወሸቁበት ያወጡታል። መቼም ቢሆን ነገሮችን አይረሱም። ባልጠበቅኸው ጊዜ፣ ባላሰብኸው ሰዓት አሳቻ ቦታ ላይ አንተን ለማጥቃት ወይ አሸናፊ ለመሆን ይጠቀሙበታል።”
ከት ብዬ ሳቅኹኝ!
“ሳቅ! ጊዜው እስኪመጣልህ ሳቅ!” ብሎ አብሮኝ ሳቀ
“የምር ግን ነገሩ ስላልገባኝ ነው”
“ለምሳሌ እኔ የሆነ ጊዜ የሆነ ነገር እላለሁ። ለምሳሌ በጭቅጭቅ መሀል “ገደል ግቢ” እላታለሁ። ከ15 ዓመት በኋላ ‘በእንዲህ በእንዲህ ጊዜ፣ እንዲህ እንዲህ ስናወራ፣ እንዲህ ስል ገደል ግቢ ብለኸኝ ነበር። እህ?’ ትለኛለች። እኔ አላስታውሰውም። ዛሬ ብለኸው በመነጋውም ትዝ ላይልህ ይችላል። በዚህ በጣም ተናደህ ‘እና ምን ይጠበስ ያልኩ እንደው?’ ትላታለህ። ነገሩ ጭራሽ ይግላል…”
“ለሁሉም ሴቶች ላይሰራ ይችላል” አልኩኝ ነገሩን ለማስቀጠል እና ትንታኔውን ለመስማት በመጋበዝ
“ቀልዴን አይደለም። ሴቶችን ለማሳነስ ብዬ አይምሰልህ። በዚህ ዙሪያ ያለኝን ግንዛቤ እና ልምድ እነግርሃለሁ። እረዳቸዋለሁ። በአብዛኛው የራሳችን የወንዶቹ ችግር ነው፤ ግድ እናጣለን። ስለሚስቴ ወይ ቀድመው ስለነበሩ ሴቶች አይደለም ማወራው። ማነጻጸሪያዬም እነሱ ብቻ አይደሉም። ከእህቶቼ ጋር፣ ከእናቴ ጋር፣ ከአያቴ ጋር፣ ከሚስቴ እናት ጋር፣ ከአጎቶቼ/አክስቶቼ ልጆች ጋር ያወራሁበት እና ያየሁት ነገር ነው። 4 እህቶች አሉኝ። ሁሉም በዚህ ጉዳይ ይስማማሉ።”
“ይገርማል። ግን ለምን እንደዚህ ይሆናል?”
“በአብዛኛው ነገሮችን በግል እንደተደረገባቸው ነው የሚወስዱት (they take things personally)። እንዲህ ስልህ ሴቶችን ከወንዶች ላሳንስ ወይ ልክ አይደሉም ልል አይደለም። ግን ተፈጥሮአቸው ይመስለኛል። በርግጥ ስለሁሉም ሴቶች እያወራሁ አይደለም። ላወራም አልችልም። ግን ከጓደኞቼም ከቤተሰቦቼም ከስራ ባልደረቦቼም ጋር በተለያየ ጊዜ አውርተነዋል። ወንዶችም ሴቶችም እንስማማበታለን። ብዙ ምርምር አድርጌያለሁ። (ሳቀ)
እድሜህ ሲገፋ ከሴቶች ጋር ብዙ ግጭት ስታስተናግድ፣ ምንድን ነው ችግሩ ማለትህ አይቀርም። ዙሪያህን ስታጤን ይገባሃል። ችግሩንም ስታወሩ ማወቅህ አይቀርም። አንተ ብዙ ስላልኖርክ ብዙ ላይገጥምህ ይችላል። ከፍቅረኛህ ጋር ተጋብታችሁ 10 ወይ 20 ዓመት ስትኖሩ የምለው ይገባሃል። ለምን አሁን አትጠይቃትም? ትነግርሃለች። ደግሞ ሲወዱህ እና አንተ አሪፍ ስትሆን ድብቅ አይደሉም።
ዛሬ የምትላትን ሁሉ የምትመዘግብበት ቦታ አላት። አስባው አይመስለኝም። እንዲሁ ተፈጥሮዋ ነው። ታውቃለህ ሴቶች ከወንዶች የበለጠ ስሜት (feelings) አላቸው። መኖር ይፈልጋሉ። ቁም ነገር እንጂ ቀልድ አይፈልጉም። ያምኑሃል። በቁም ነገር ይሰሙሃል። ስለዚህ አይረሱትም።
አንተ በ30 ቀናት 30 ጊዜ ፋክ ዩ ትላለህ። ብርጭቆው ሲወድቅ፣ ቀጠሮ ሲረፍድብህ፣ ጓደኛህ ሲያስቀይምህ በተለያዩ አጋጣሚዎች ተናደህ ምታወጣው ቃል አለ። ጓደኞችህን ሃምሳ ጊዜ ትላቸዋለህ። ጉዳያቸውም አይደለም። ሚስትህን ግን ልትሸውዳት አትችልም። ለእሷ ያልክበትን አጋጣሚ አትረሳውም። በግጭታችሁም ጊዜ ሁሉ ወደ ኋላ የሆነ ዓመት ተጉዛ የሆነ ትውስታ ትመዛለች።”
አሁንም ከት ከት ብዬ ሳቅኹኝ።
“ሳቅ አንተ። አሁን ሳቅ።” ብሎኝ ሳቄን ተቀብሎኝ ቀጠለው።
አባባሉ አስቆኝ እንደገና ሳቅኹኝ።
“ምሳሌ ልንገርህ” ብሎ ቀጠለ። በሚያወራው ነገር ሁሉ ምሳሌ አያጣም። የእናቴን በነገር ሁሉ የሚነገሩ ተረቶች ያስታውሰኛል።
“አንዴ የሚስቴ እናት ጉዞ ነበራት እና አውሮፕላን ማረፊያ እንዳደርሳት ጠየቀችኝ። ለጉዞዋ መገኘት ያለባት ከሰዓት 8 ሰዐት ነው። ላደርሳት ከተስማማሁ በኋላ ከሰዓቱ እንዳላረፍድባት አስጠንቅቃ ነግራኛለች። እንደተቀጣጠርነው ከቀኑ 6 ሰዐት ተኩል ላይ ቤቷ ደረስኩ።
‘እንሂድ’ ስላት፥
‘ቆይ አንዴ፣ እንዲህ ተዝረክርኬ እንዴት እሄዳለሁ?’ ብላ መኳኳል መቀባባት ጀመረች (በእጁ ፊቱ ላይ አቀባቧን እያሳየኝ)
‘በቃ ምንም አትሆኚ እዚያ ስትደርሺ ሆቴልሽ ትስተካከያለሽ፣ ይረፍድብሻል’ ብላት
‘እምቢ አሻፈረኝ! እኔ ነኝ ተጓዧ አንተ?’ አለች። ሰዐቷን አይታ ችግር የለም እንደርሳለን አለችኝ።
በመከራ ሰባት ሰዐት ላይ ወጣች እና ጉዞ ጀመርን።
የባለቤቴ እናት በሁሉም ነገር ላይ አውቃለሁ ባይ ናት። ምንም ነገር ብታደርግ አስተያየት ትሰጥሃለች። ምንም ነገር!
እንደልማዷ ገና ስነሳ፥ “ኧረ ቀስ!” ብላ ጀምራ አነዳዴን መተቸት ጀመረች። በርግጥ ሰዐቷ እንዳይረፍድ ብዬ እየተዋከብኩ ነበር። ፈጥኜ ለመንዳት ሞክሬያለሁ።
መሀል ላይ ምንጭቅ ብላ ደጋግማ ቀስ እንድል ትነግረኛለች፤ ‘መድረስ አለብሽ በሰዐትሽ’ ብዬ ላስረዳት እሞክራለሁ። በጣም ጨንቆኛል ለእሷ።
እሷ ደግሞ ዘና ብላ ‘ገና ነው እንደርሳለን’ ትለኛለች።
መሀል ላይ ጭቅጭቋ ከአቅም በላይ ሆነብኝ። ካላስቆምኳት አደጋ ላይ ሁሉ ልትጥለኝ በምትችል መልኩ ትናገራለች።
ዳር አቁሜ ‘የእኔ እናት፥ ካልፈለግሽ ውረጂና ታክሲ ጠርተሽ ሂጂ።’ አልኳት።
አበደች። እንዴት ብትደፍረኝ አለች።
‘ነግሬሻለሁ ምርጫው ያንቺ ነው።’ አልኳት። የምር ተናድጄ ነበር።
አማራጭ ስለሌላት የግዷን ተሳፍራ አፏን ዘግታ ሄድን። ስንደርስ 20 ደቂቃ አርፍደናል። እድለኛ ሆና ግን አውሮፕላኑ አረፈደና ተሳፈረች።
ከዚያ ምን ቢሆን ጥሩ ነው? ከ10፣ ልክ ድፍን 10 ዓመት በኋላ የሆነ ክርክር ይዘን መሀል ላይ፥ ‘ግን ለምን ነበር ወደ ፈረንሳይ ስሄድ ከታክሲ ላይ እንዲያ ያበሻቀጥከኝ?’ አለች። (አብረን ሳቅን)
ምን አገናኘው? ምን ልበላት? እኔ ከዚያ ቀን በኋላ ትዝ ብሎኝም አያውቅም። ያልኩትን ብያት አብቅቷል። ያን ያለችው የተነሳውን ክርክር በባሌም በቦሌም ለማሸነፍ ስለፈለገች ነው። የሚስትህ እናት ስለሆንኩ፣ እንዲህ ስለሆነ፣ ያኔ ታክሲ ያዢ ስላልኸኝ ብላ ልታሸማቅቀኝ ስተፈልግ ነው።
አይገርምም? እንደዚህ ዓይነት ነገሮች ይገጥሙሃል። የፈለግኸውን ባለትዳር ጠይቅ ይነግሩሃል።”
ሳቅ ብዬ፥ “ይገርማል፤ ግን…” ስለው
“ሌላ ምሳሌ ልንገርህ፥ እናቴ እስክትሞት ድረስ ከአንድ ወንድሟ ጋር እስከዚህም ነበሩ። 20 ዓመታት ተደባብረው ነው ያሳለፉት።
ምክንያቱን ገምት! እናታቸው በጣም ውድ የሆኑ ዘርፍ ያላቸው፣ የእምፑል ማቀፊያዎች ነበሯት። እጅግ በጣም ውድ ነበሩ። እና ለእናቴ እንድትወስዳቸው ቃል ገብታላት ነበር። እናቴ ስትሞት ወንድሟ ልቡ እያወቀ በጉልበቱ ወሰዳቸው።
የእርሷ እንደሆነ ነግራው ልታስረዳው ሞክራ ነበር። ግን ብዙም ግድ ያለው ዓይነት አልነበረምና ዝም ብሏት ወሰደው። ተቀየመችው። ግንኙነታቸውም እስከዚህም ሆነ። እሱ ለምን እንደሆነ አያውቅም ነበር። አይገባውም።
ከ20 ዓመታት በኋላ እሱም በሰል ብሎ፣ እሷም ደከም ብላ ግድ ሲነጋገሩ አስታወሰችው። ፀፀቱ ሊገድለው ደረሰ። በጣም አዘነ።”
ነገሩንም ለማብሰልሰል እየሞከርኩ፥ ሳቅ ብዬ “ይገርማል! እና ከሚስትህም ጋር እንዲህ የድሮ ነገር እያስታወሰችብህ መግባባት እያቃታችሁ ነው?” ብዬ ጠየቅኹት
ይቀጥላል…
እውነት ነው ወይ?

ዮሐንስ ሞላ's Blog
- ዮሐንስ ሞላ's profile
- 3 followers
