ሱስቆት…

[image error]ፌስቡክ ከናፍቆት መወጣጫ፣ ከመረጃ መለዋወጫ እና ከድድ ማስጫ ተግባሩ ጋር ፍቅር አስይዞን፣ ዞር ሲሉ ናፍቆት ቢጤ እየወዘወዘንና ቢያስመስለውም፣ ነገሩ ከፍቅር እና ናፍቆት በራቀ መልኩ ሱስ መሆኑ ሲሰማኝና፣ ችግሩን ለመቅረፍ መለማመድ እንዳለብኝ ወስኜ የነበረ ቢሆንም ቅሉ፥ እስኪ ይህንን “ልጻፍ እስኪ” ብዬ ፌስቡክ ላይ ለመቆየት ጥሩ መላ ዘየድኩኝ። ይህን ጽፌም ላሽ ብል ኖሮ፥ ጥሩ! ግን የስራው ጸባይ፥ ተመላልሶ አስተያየት ማንበብንና፣ ባለጌዎችን እያሳደዱ ማስወገድም ያካትታልና መክረማችን ነው። ሄሄሄ…


 


ሰሞኑን አገር ቤት ኢንተርኔት ከመቋረጡ ጋር ተያይዞ፥ ወዳጆች የፌስቡክ እና የሌሎች ማኅበራዊ ድረ ገጾች “ናፍቆት” እንዴት እንዴት እንዳደረጋቸው እያየን ነው። እኔም “መቼም የሸገር ጓዶቼ በሰፊው ብትን ያላሉበት ፌስቡክስ ቢቀር ይሻላል” ብዬ፥ ከፌስቡክ ለመራቅ ያደረግኩት ሙከራ ባጭሩ ሲከሽፍብኝና፣ ጣቴን እየበላኝ በባዶ ሜዳም… “ሄድኩ” ስል ስመለስ ከራሴ ጋር እየተሳሳቅኹኝም


 


“ኧረ ይኼ ነገር የከፋ ሳይሆን አልቀረም።” ብዬ “ከፌስቡክ ሱስ መላቀቂያ መንገዶች”ን በመፈለግ፣ በዚያውም ስለፌስቡክ እና ስለሱሱ ማንበብ ቀጠልኩ። (ሱስ የመሆኑ ብዛት፥ ሰው ሁሉ መጠቀም ቢያቆም እንኳን ብቻችንን መጥተን እንድናውደለድል የሚገፋፋን ስሜት አለ።) የሚገርመው ነገር ግን፥ መላቀቂያ መንገዶቹን እያነበብኩ ራሱ፣ በየመሀሉ ስንት ጊዜ ፌስቡኬን ቼክ እንዳደረግኩ እኔና እግዜሩ እናውቃለን። ሃሃሃ…


 


የተጠቆሙትን መንገዶች ሁሉ ሳነብ፥ በልጅነት “እስክሪብቶዬ የዛሬን ጻፊልኝ፣ ለነገ አስገዛለሁ” ብለን ቁልቁል ዘቅዝቀን እንደምናራግፋት፣ “ቆይ አሁን፣ ቆይ በኋላ፣ ቆይ ነገ” ስል፥ ባህሩ እሹሩሩ እያለኝ እንደሆነ በደንብ ገባኝ። “ወደ ሲዖል የሚወስዱ መንገዶች በማስተባበያ የተጠረጉ ናቸው።” (the road to hell is paved with excuses) እንዲል ፈረንጅ፥ ሳልቦዝን፥ ለማስተባበያዎቼ ሳይቀር ማስተባበያ ስፈልግ ቆየሁ።


 


በንባቤ መሀል “ድረ ገጾቹን ብሎክ ማድረግ” የሚል ጥቆማ ሳገኝ፥ “wow, this must be working” ብዬ blocksiteን ተጠቅሜ ብሎክ አደረግኩት። ችግሩ እየረሳሁት ብቅ ስል፥ አውቶ ፖፓፑ ሲያላግጥኝና ስስቅ ዋልኩ። ስቄም አላባራሁ። ከዚያም ቆይ የፌስቡክን ሱስ ለማስታመም እና ቀስ በቀስ ለመተው ብዬ፣ ተያያዥ ነገሮችን እያየሁ ለመቆየት ወሰንኩና፥ ‘how to unblock a site blocked by a blocksite’ ብዬ ፈለግኩና ማብሪያና ማጥፊያዋን (the switch) አገኘኋትና፥ ይኸው ቀጥታ ከመጠቀም በማብሪያና ማጥፊያ ወደመጠቀም ተዘዋውሬያለሁ።


 


“ሲጋራም ቢሆን ባንዴ ማቆም ጥሩ አይደለም። ከፓኬት ወደ 10፣ ከ10 ወደ 5 ነው” የሚሉትን አስታውሼ፥ ብሎክሳይቷን በፈረቃ አብቃቅቼ ለመጠቀም ወሰንኩና “ቆይ የዛሬን” ብዬ off አደረግኩት።
 •  0 comments  •  flag
Share on Twitter
Published on June 07, 2017 12:48
No comments have been added yet.


ዮሐንስ ሞላ's Blog

ዮሐንስ ሞላ
ዮሐንስ ሞላ isn't a Goodreads Author (yet), but they do have a blog, so here are some recent posts imported from their feed.
Follow ዮሐንስ ሞላ's blog with rss.