“…”

የሕዝብ ጩኸት ቢገፋ፣

የንጹህ ሰው ደም ቢደፋ

‘ምድር’ ሲባል ርቆ መጥቆ


ሰማያቱን ሰነጣጥቆ፥


ይጮኻል በልዩ ግርማ፣


ይሰማል በእዮር፣ ራማ፤

የሰው ስጋ ተፈትቶ፣


አይቀርም በብላሽ ከቶ፣


የኀዘን መቀነትን ፈትቶ፣


ዋይታ ነዝቶ፣ ዕንባ አራጭቶ፤


 


ከበደል ጋር ተመዝኖ፣


የክብሩን አክሊል ጭኖ፣


ከሰማይ ምኩራብ ዳምኖ፣


ዶፍ ይዘንባል


ለገፊዎች መአት ሆኖ፣


ለተገፊ ምህረት ገንኖ፤


 


ንጹሕ ቢወድቅ ሺ ይነሳል፣


ሺ ያቆማል፣ ሺ ይጠራል፤


ንጹሕ ቢጮህ ሺ ያነቃል፣


ሺ ይጣራል፣ ሺ ይሰማል፤


ንጹሕ ደምቶ ሺው ፀአዳ፣


ተሸላልሞ በፍቅር ዕዳ፤


 


የንጹሕ ደም ከእንባ ገጥሞ፥


ሰማየ ሰማያት ከርሞ፣


ወደ ምድር ሲከነበል፣


ሺ ይጠርጋል፣


ሺ ያጸዳል፤


ሺ ያቀናል፣


ሺ ያሰምጣል…


 


ወዮ ላንተ ለገዳዩ…


ግዳይ ጥለህ ስትጨፍር፥


ለሚረግጥህ ተከታዩ፣


ያፈራኸው በክፋትህ፣


ያቀናኸው በግፋትህ!


 


የበደል ጽዋህ ሲሞላ፣


ትንሳኤው ሲበሰር የሰው


በሀሴት ፋሲካው ሲበላ፣


አንተ ትኖራለህ ወድቀህ፣


ተዘርረህ በሞት ጥላ።  


 


/ዮሐንስ ሞላ/



 •  0 comments  •  flag
Share on Twitter
Published on August 08, 2016 19:55
No comments have been added yet.


ዮሐንስ ሞላ's Blog

ዮሐንስ ሞላ
ዮሐንስ ሞላ isn't a Goodreads Author (yet), but they do have a blog, so here are some recent posts imported from their feed.
Follow ዮሐንስ ሞላ's blog with rss.