‘የአስተማሪ ምግብ…’

ዩኒቨርስቲ አስተምር የነበረ ጊዜ…


 


ከእለታት ባንዱ ቀን ቡና ልጠጣ ወጥቼ ጠረጴዛ የተጋራኋቸው ሁለት ባልደረቦቼ ብስጭትጭት ብለው ሲያወሩ ሰማኋቸው።


 


“ምንድን ነው እሱ?” አልኩኝ ከመቀመጤ።


 


“እንዴት እንዴት እንደጠገቡ እኮ…” አለኝ አንዱ።


 


(በኋላ ግራ ቀኙን ስቃርም የገባኝ ሁሉም በየጠረጴዛው ያወራ የነበረው ይህንኑ ጉዳይ ነበር።)


 


“እነማን ናቸው ደግሞ?”


 


“ሌላ ማን ይሆናል? እነዚህ የተረገሙ ናቸዋ”ብሎ ተማሪዎች ወደሚራመዱበት አቅጣጫ አገጩን ቆለመመው።


 


“ተማሪዎቹ? …ምን ተባለ ደግሞ?” አልኩት እንዲህ መነጋገሪያ የሆነውን ጉዳይ ለመስማት አቆብቁቤ።


 


“እዚህ ላውንጅማ ድርሽ አይሏትም። እንደውም በዲሲፕሊን ኮሚቴ መከሰስ አለባቸው።” አለኝ።


 


“ጋይስ እኛም እኮ መምህራን ነን። እንስማውና አብረን እንቃጠል።” አልኩ።


 


“ምን ባክህ፥ ሁለት ሴቶች ከውስጥ እየወጡ፣ አንዲት ጓደኛቸውን… ‘ተመለሽ ተመለሽ፥ ምግብ አልቋል’ አሏት። ‘ምንም’ ስትል፥ ‘አይ ያለው ለአስተማሪ የሚሆን ብቻ ነው’ አሏት። እንዲሰማ ጮክ ብላ…” አለኝ።


 


አተራረካቸውና አበሰጫጨታቸው ዘና አድርጎኝ ስለነበር፥ “እንግዲህ ተማሪዎች ላውንጅ ሄዶ በልቶ፣ የተማሪን ምግብ የመግዛት አቅም አለን ማለት ነው። በፊት እንኳን፥ አንዱ ጋ ለትምህርት ሲኬድ የፈረደባት ካሪና ተገዝታ “እኔም ተምሬ መጣሁ” አስብላ ታስሸልል ነበር።” ብዬ እንደመሳቅ አልኩ። አልሳቁልኝም። ተናደዋል።


 


እንግዲህ “ለአስተማሪ የሚሆን ለተማሪ የማይሆን” (that teachers can’t afford, but students) የምግብ ዓይነት መኖሩ ነበር እንዲያ ያተከናቸው።


 


ቀን ተቆጥሮ ተማሪዎቹም ተከሰሱ አሉ።


 


“ሁለተኛ እንዳይለመዳችሁ” ተብለው በማስጠንቀቂያ ደብዳቤ ሳይቆነጠጡም አልቀሩም። ወዲያውም፥ የካፌው በራፍ ላይ “ለተማሪዎች አይፈቀድም” ዓይነት ትኩስ ማስታወቂያ ተለጥፎ ነበር።


 


ይኸው ባለፈው ወር የመምህራን ደመወዝ መጨመሩን ሰምተን


 


“እኛ ማስተማር ስናቆምማ የማይሻሻል ነገር የለም” የሚል ቅናት ባይሸነቁጠንም፥…[image error]


 


መንግስት የሆነ ያህል መቶ ብር “ጨመርኩ” ያለ ጊዜ፥ ከወሬው እኩል፥ የቤት አከራዮቻችን የጨመሩብን ብር ትዝ ብሎኛል። በዚያ ሰሞን ነጋዴዎች እንዴት እንዴት እንደሆኑም አይረሳኝም።


 


እና ጓዶች ጭማሪው ከወጪ ቀሪ እንዴት ነው?


 


ከተማሪ ጋር ያጋፋል?


 


የተማሪን የምግብ ምርጫ ያስቀምሳል?


 


የገቢ ግብር ማሻሻያ አዋጅም ከሀምሌ 1 ጀምሮ በሚገኝ ገቢ ላይ ተፈጻሚ እንዲሆን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባስቸኳይ በጠራው ስብሰባ ላይ አዋጅ አጽድቋል አሉ። ምን አስቸኮላቸው?[image error]


 


በነገራችን ላይ፥ ዜናው ላይ የተዘገበው ከቅጥር እና ከኪራይ ለሚገኙ ገቢዎች ነው። ከንግድ ስለሚገኙ ገቢዎች የተባለ ነገር የለም። የተጨማሪ እሴት ታክሱ እንደው ዞሮ ሸማቹ ላይ የሚጨመር ነውና በተዘዋዋሪ ተቀጣሪውን ነው የሚመለከተው። #Ethiopia



ሰላም!

 •  0 comments  •  flag
Share on Twitter
Published on July 26, 2016 20:07
No comments have been added yet.


ዮሐንስ ሞላ's Blog

ዮሐንስ ሞላ
ዮሐንስ ሞላ isn't a Goodreads Author (yet), but they do have a blog, so here are some recent posts imported from their feed.
Follow ዮሐንስ ሞላ's blog with rss.