እንዳለጌታ ከበደ's Blog
September 22, 2013
‹አንበሳው› ማን ነው፤ ‹አህያውስ› የምን ምሳሌ?
የታወቀ ነው፤ የተለመደ! በየተረቶቻችንና ሥነ-ቃሎቻችን አንበሳ መሪ ተዋናይ ነው፤ ያለእሱ መድረኩ አይደምቅም፤ ምልልሱ አይሞቅም፤ በተቃራኒው ደግሞ አህያን ረዳት ተዋናይ አድርገን ልንቆጥረው እንችላለን፤ ቢኖር ያገለግላል ባይኖር ደግሞ ብዙም አያጐድል ተብሎ ችላ የሚባል፡፡
ይኼ መጣጥፍ በሕይወት መድረክ ላይ ሁለቱንም ሆነን የመተወን እድል ስለገጠመን ሰዎች ለመተረክ የሚሞክር ነው፤ አንበሳ ሆነን ወይም ተብለን በህይወት ሳለን ስለተፈራን ሞተን ስንገኝ ደግሞ ሐውልት ስለቆመልን ሰዎች፤ አህያ ሆነን ወይም ተብለን በህይወት ሳለን በጫንቃችን ላይ ውርደት በጭንቅላታችን ላይ ስቅየት ስለተፈራረቀብን፤ ሞተን ስንገኝ ደግሞ ለማንም ጥንብ ጐታች ስለምንሰጥ ሰዎች የሚተርክ…እውነት ነው አንበሳ መሆን ደስ ይላል፤ ‹ሞኣ አንበሳ ዘእምነገደ ይሁዳ…› መባል ደስ ይላል፤ አንበሳ ምሳሌነቱ ከድሮ ጀምሮ ለተወደደ እና ለተከበረ ነገር ነው፤ ኢየሱስም ከይሁዳ ዘር ነው ብለን ዘር ማንዘሩን እንቆጥራለን፤ ከአንበሳው ወገን የሚመደብ! እናም የፊተኞቹ ነገሥታት ‹አንበሳነት ከጥንት ጀምሮ በደማችን የተዋኸደ ነው› ለማለት፤ የተቀደሰውን ነገር ‹ያደግንበት ነው› ለማለት፤ ‹ሞኣ አንበሳ…› ይላሉ፤ መጽሐፍ ቅዱስ በአንድ በኩል አንበሳን እንዲህ ለተባረከ ነገር አሳልፎ ሲሰጠው፤ በሌላ ምዕራፍ ላይ ደግሞ አንበሳን በዲያብሎስ ይመስለዋል፤ በነጣቂ፣ በአስጨናቂ፣ በእንቅልፍና በእረፍት ሰራቂ!እናም እንዲህ እላለሁ፤ የሀገራችንና የአሕጉራችን ቀደምትና የአሁን መሪዎች ‹አንበሳ›ነን ብለው ራሳቸውን ሲመስሉ የትኛውን ዓይነት አንበሳ ሆነው አግኝተናቸዋል?…ከቅዱሳት መጽሕፍት ውጪ፤ አንበሳ በየተረቱ ውስጥ ድል አድራጊ ነው፤ አንድም አውሬ እፊቱ ይቆም ዘንድ አይቻለውም፤ ‹ንጉሥ› ነው፤ ቀጪ እና ተቆጪ የለውም፤ ንዴቱ ዛፎቹን ያንቀጠቅጣል፤ ተራሮችን ያርዳል፤ እጁ ውስጥ ከገባን ከመዳፉ ፈልቅቆ የሚወስደን ሃይል ማን ነው?... በርግጥ ይህ ሁሉ ሃይል አንበሳው ስልጣን ላይ እስካለ ነው፤ ስልጣኑ የሚጠናቀቀው ደግሞ የጉብዝና ወራቱና የወራት ዘመኑ ሲያከትም ነው፤ ከዚያ በኋላማ፤ ዝንቦች መጫወቻ ያደርጉታል፡፡
ይኼ መጣጥፍ በሕይወት መድረክ ላይ ሁለቱንም ሆነን የመተወን እድል ስለገጠመን ሰዎች ለመተረክ የሚሞክር ነው፤ አንበሳ ሆነን ወይም ተብለን በህይወት ሳለን ስለተፈራን ሞተን ስንገኝ ደግሞ ሐውልት ስለቆመልን ሰዎች፤ አህያ ሆነን ወይም ተብለን በህይወት ሳለን በጫንቃችን ላይ ውርደት በጭንቅላታችን ላይ ስቅየት ስለተፈራረቀብን፤ ሞተን ስንገኝ ደግሞ ለማንም ጥንብ ጐታች ስለምንሰጥ ሰዎች የሚተርክ…እውነት ነው አንበሳ መሆን ደስ ይላል፤ ‹ሞኣ አንበሳ ዘእምነገደ ይሁዳ…› መባል ደስ ይላል፤ አንበሳ ምሳሌነቱ ከድሮ ጀምሮ ለተወደደ እና ለተከበረ ነገር ነው፤ ኢየሱስም ከይሁዳ ዘር ነው ብለን ዘር ማንዘሩን እንቆጥራለን፤ ከአንበሳው ወገን የሚመደብ! እናም የፊተኞቹ ነገሥታት ‹አንበሳነት ከጥንት ጀምሮ በደማችን የተዋኸደ ነው› ለማለት፤ የተቀደሰውን ነገር ‹ያደግንበት ነው› ለማለት፤ ‹ሞኣ አንበሳ…› ይላሉ፤ መጽሐፍ ቅዱስ በአንድ በኩል አንበሳን እንዲህ ለተባረከ ነገር አሳልፎ ሲሰጠው፤ በሌላ ምዕራፍ ላይ ደግሞ አንበሳን በዲያብሎስ ይመስለዋል፤ በነጣቂ፣ በአስጨናቂ፣ በእንቅልፍና በእረፍት ሰራቂ!እናም እንዲህ እላለሁ፤ የሀገራችንና የአሕጉራችን ቀደምትና የአሁን መሪዎች ‹አንበሳ›ነን ብለው ራሳቸውን ሲመስሉ የትኛውን ዓይነት አንበሳ ሆነው አግኝተናቸዋል?…ከቅዱሳት መጽሕፍት ውጪ፤ አንበሳ በየተረቱ ውስጥ ድል አድራጊ ነው፤ አንድም አውሬ እፊቱ ይቆም ዘንድ አይቻለውም፤ ‹ንጉሥ› ነው፤ ቀጪ እና ተቆጪ የለውም፤ ንዴቱ ዛፎቹን ያንቀጠቅጣል፤ ተራሮችን ያርዳል፤ እጁ ውስጥ ከገባን ከመዳፉ ፈልቅቆ የሚወስደን ሃይል ማን ነው?... በርግጥ ይህ ሁሉ ሃይል አንበሳው ስልጣን ላይ እስካለ ነው፤ ስልጣኑ የሚጠናቀቀው ደግሞ የጉብዝና ወራቱና የወራት ዘመኑ ሲያከትም ነው፤ ከዚያ በኋላማ፤ ዝንቦች መጫወቻ ያደርጉታል፡፡
Published on September 22, 2013 06:32
September 20, 2013
እጃችሁ በደም ተነክሩዋል….
እጃችሁ በደም ተነክሯል….…ወደ ኦሪታውያኑ ዘመን ልመልሳችሁ፤ ከዚያ ዘመን ውስጥ ፈርኦንን፣ ሙሴንና ኢያሱን እናንሣ፤ እነዚህን ሰዎች ደግሞ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ እንፈልጋቸው፤ የእነዚህ ቢጤዎች ናቸውና ዛሬ እንደጨቋኝ ገዢ ተቆጥረው የወቀሳ ናዳ የሚዘንብባቸው፤ የእነዚህ ቢጤዎች ናቸውና ዛሬ ከጭቆና ነፃ እንዳወጡን ተነግሮ የሰማዕት ሀውልት እንዲቆምላቸው የሚደረገው፤ የእነዚህ ቢጤዎች ናቸውና ዛሬ በህይወት ኖረው÷ ከወንድሞቻቸው የተቀበሉትን የትግል ዓርማ ከፍ አድርገው የተስፋይቱን ምድር እንዲጐበኙ የፍትህ አምላክ ስለ ፈቀደላቸው ደስ የምንሰኝባቸው!…‹ያ› የምንለው ትውልድ ተገልጦና ተነብቦ የማያልቅ መጽሐፍ እየሆነ ነው፤ ውለን ባደርን ቁጥር ተድበስብሰው የታለፉና ተቆፍረው የተቀበሩ ጉዶችና ገድሎችን እያደመጥን ነው፤ ያንን ትውልድ የሚያጀግኑ መዝሙሮች መስማት ብቻ ሳይሆን፤ የትውልዱን አካሄድ የሚነቅፉ ብዕረኞችም በየህትመት ሚዲያው ብቅ ብቅ እያሉ ነው፤ እነዚህ ብዕረኞች ትውልዱን ጀብደኛ ነበረ ነው የሚሉት፤ ከውጭ ሀገር የተኮረጀ ርዕዮት ይዞ ስለተነሣ ነው ተሰናክሎ የወደቀው ነው የሚሉት፤ ሕዝቡ የኔ ነው ብሎ የሚያምንበትን አምላኩን ከልቡ ለማስወጣት ይታገል ነበር ነው የሚሉት፤ ብዙ የሚሉት ነገር አላቸው፤ እንዲህ በማለታቸው አንዳንድ የያ ትውልድ አባላት ተቺዎቻቸውን ተቆጥተዋል፤ ሣታውቁን ነው የምትዘባርቁት ብለዋል፡፡ ጉዳዩ አጨቃጫቂ ነው፤ ክርክርና ንትርኩም የሚቀጥል! ያ ትውልድ ሜዳው ሰፊ ነው፤ በዚህ ሰፊ ሜዳ ላይ በ1960ዎቹና 70ዎቹ መጀመሪያ የነበሩ ወጣቶች ተጋጥመውበታል፤ ተጋጣሚዎቹ የማይከሰስና የማይወቀስ የሆነውን ንጉሳዊ አገዛዝን ገርስሰው ጥለዋል፤ የማይነካውን ከደፈሩ በኋላ ግን እርስ በርስ ተበላሉ፤ እርስ በርስ ተዋዋጡ፤ አብዮቱ ‹አፋጀሽኝ›ን ሆነ፤ መቧደናቸው ቀጠለ፤ ሞት፣ ስደት እና እስር የሁሉንም ቤት ለመጐብኘት ትጥቁን አጠበቀ፤ ደርግም፣ ኢሕአፓም፣ ሕወሓትም፣ መኢሶንም… ወዘተርፈው በሙሉ ልቡን ወያኔ አደረገ፤ ሸፈተ፤ ከተማውም ገጠሩም ዱሩም ገደሉም የእዚህ ትውልድ መሸሸጊያ ሆነ…
Published on September 20, 2013 09:21
September 19, 2013
ያልተቀበልናቸው (2)
ይኼ የ ‹ያ ትውልድ› ውጤት ነው፤ ከ1950ዎቹ ወዲህ (ከታህሳስ ግርግር በኋላ) በተፈጠረው የፖለቲካ ትኩሳት ሰበብ፤ እነ ጥላሁን ገሠሠ (ድምፃዊ) ለመጀመሪያ ጊዜ ከአማርኛ ቋንቋ ውጪ አይደፈር የነበረውን በኦሮምኛ ቋንቋ ዘፍነው በሸክላ አስቀረፁ፤ እነ መኃሙድ አህመድ (ድምፃዊ) የጉራጊኛ ዘፈን አስደመጡ፤ ቀስ በቀስ ሌሎች ተከተሉ፤ አፍ መፍቻ ቋንቋቸው አማርኛ ያልሆነ ደራሲዎች መነበብ ጀመሩ - ጸጋዬ ገ/መድህን ከአምቦ÷ ስብሃት ገ/እግዚአብሔር ከአድዋ÷ ሰሎሞን ደሬሣ ከወለጋ÷ ሳህለሥላሴ ብርሃነማርያም ከእምድበር÷ አማረ ማሞ ከሲዳሞ… በኢህአዴግ ዘመን ደግሞ አንዱን ብሄር መርጦ፣ አንዱን ማኅበረሰብ ለይቶ ራሱንም የተዘፈነለትን አካባቢም የሚያስተዋውቅ ድምጻዊ በዛ፤ ዘፈኖቹ በአብዛኛው ተመሳሳይና ተደጋጋሚ ይዘት ያላቸው (የሆነ ሰው፣ የሆነ ቦታ ሄዶ፣ የሆነች ሴት ዓይቶ፣ በፍቅሯ ተማርኮ ‹አንቺን ካገኘሁ አዲስ አበባ ለምኔ› የሚሉ፤ ከግጥሙ ይዘት ይልቅ ለአጨፋፈር ስልታቸው ቅድሚያ የሚሰጡ) ቢሆኑም፤ የተጫወቱት ሚና እና ሚዲያው የሚሰጣቸው ሽፋን ቀላል አይደለም፡፡ የኦሮሞዎች ‹እሬቻ›ን፣ የሲዳማዎች ‹ጨምበላላ›ን፣ የትግራይ ክልል አካባቢ ነዋሪዎችን ‹ሻደይ›ን ማክበራቸውም ጥሩ ነው - እዚህ ደረጃ ለመድረስ ጥርጥር የለውም ብዙ ዋጋ ተከፍሏል፤ ሆኖም ግን ነጠላ ዜማ ስለተለቀቀለትና አንድ ትውፊታዊ በዐሉ ስለተከበረለት አንድ ብሄር ማንነቱ ታወቀለት ማለት አይደለም፤ ይሄ ብቻ በቂ አይደለም፤ ማንነት በዳንስ ብቻ አይለካም፤ በብሄር-ብሄረሰቦች ቀን እንዲታደሙ ስለተጋበዙ ብቻ ሙሉ ማንነታቸው ታውቆላቸዋል ማለት ስህተት ነው፤ ማንነት በጥልቀት የሚታይ መሆን አለበት እንጂ፤ እንደ ብሄራዊ ቴአትር ባለ አገር ፍቅር መድረክ አኗኗራቸው በጨረፍታም ቢሆን የሚታይ መሆን አለበት እንጂ፤ እንዲሁ ስለተዘፈነላቸውና ዳንስ ማሳያ መድረክ ስለተዘረጋላቸው የችግሮቻቸው ቀዳዳ ተደፈነ ማለት አይደለም፡፡
በብሄር ብሄረሰቦች ቀን ‹ጥሩዋቸው እስኪ እነዚያን ጥቁሮች! ሞቅ ሞቅ ያድርጉት በዐሉን› ተብለው የቀረቡ ነው የሚመስሉት፡፡ ይሄ አይደንቅም ወይም አይደንቀኝም፤ በበዓል ቀን የቅርብ ብቻ ሳይሆን የሩቅ ሰውም ይጋበዛል፤ ወዳጅ ዘመድ ይታደማል፤ ፊታውራሪውም፣ በረንዳ አዳሪውም ይጠራል፤ የነዚህ የተናቁ፣ የተረሱ፣ የማናውቃቸውና እንደ መጤ የምንቆጥራቸው ኢትዮጵያውያን በዓመት አንድ ቀን ‹በየማጌጫችሁ ተሽሞንሙናችሁ ቅረቡ› ብሎ መጋበዝ ‹የእኩልነት መብታቸው መረጋገጡን› አያሳይም፤ የሚያስፈልገው እነሱን ለአደባባይ ማብቃት ነው፤ የተዘጋባቸው የዕውቀት፣ የስልጣንና የስልጣኔ ብቻ ሳይሆን የሰብዓዊ መብቶች በር እንዲከፈትላቸው ማድረግ ነው፡፡አዲሳባ ፒያሳ እምብርት ላይ አንድ ማስታወቂያ አይቼ ነበር ‹ስክሪን› ላይ የሚተላለፍ፡፡ ስክሪኑ ላይ የአማራ አለባበስ የለበሰች አንዲት ሴት ታልፋለች - ‹አማራ ነኝ፤ በአማራነቴ እኮራለሁ› ትላለች፤ ትግሬዋም፣ ኦሮሞዋም፣ ሶማሌዋም፣ ሀደሬዋም… ሁሉም እየመጡ ይሄዳሉ፤ የብሄራቸውን ስም ጠቅሰው ‹እኮራለሁ!› የሚል መልእክት አስከትለው፡፡ ከዚያም አንዲት ሴት ትመጣለች (?)፤ ‹ደቡብ ነኝ፤ በደቡብነቴ እኮራለሁ› የምትል፡፡ ያነበብኩት ቀን በጣም ነው በፌዴሬሽን ምክር ቤቱ ያፈርኩት - ደቡብ የብሄር ስም ነው እንዴ? ወይስ ማን የሁሉንም ስም ሲዘረዝር ይውላል ለማለት ነው?... ደቡብ የአቅጣጫ ስም ነው፤ በደቡብነቴ እኮራለሁ ማለት ምንድነው? አንዲት ሴት እንዴት ከ45 ያላነሱ ብሄሮችን ወክላ ትቀርባለች? ይኼ የተወሰኑ ሰዎችን ስም ጠቅሶ የተቀሩትን ወዘተረፈ ብሎ ከማጠቃለል በምን ይተናነሳል?) …ኢትዮጵያ ውስጥ እጅጉን ከሚደንቁኝ ነገሮች መካከል፤ ከጋምቤላ አካባቢ የሚመጡ ሰዎችን የምናይበት ዓይን የተንሸዋረረ መሆኑ ነው…አንድ ቀን÷ ከአንድ የቅርብ ወዳጄ ጋር አመሸሁ፤ ምሽቱ እየገፋ ሲሄድ፤ እኔ ደግሞ ሌላ የማውቀው ሰው ገጠመኝና የናፍቆት ሰላምታ ስለዋወጥ፤ ሰላምታው የረዘመበት ወዳጄ ‹መጣሁ› አለኝና ከወንበሩ ተነሣ፤ ከኛ ፈንጠር ብሎ ወደተቀመጠው ሰው በአገጩ አመላከተኝ፤ ሰውየው ጥቁር ነው፤ ብቻውን ቢራውን ይዞ እየተዝናና ነው፤ ዓይኑን በመደነስ ላይ በሚገኙ ወይዛዝርት ላይ አነጣጥሯል፤ ወዳጄ ‹መጣሁ እስኪ፤ ይህን ጥቁር አፍሪካዊ ላዋራው፤ አጋጣሚውን በመጠቀም የእንግሊዝኛ ቋንቋ ችሎታዬን ላሻሽል› አለና ሄደ፤ የሚነጋገሩት ይሰማኛል፤ ወዳጄ ጥቁሩን ሰው ለማጫወት በብርቱ እየተጋ ቢሆንም፣ ከየት እንደመጣ ቢጠይቀውም፣ ኢትዮጵያን እንዴት እንዳገኛት ቢያነጋግረውም፣ የወይዛዝርቱ ዳንስ የፈጠረበትን ስሜት እንዲያጫውተው ቢጐተጉተውም… ጥቁሩ ሰው ግን አልመለሰለትም፡፡ በመጨረሻም ሲበዛበት ጊዜ ብድግ ብሎ ‹‹እናንተ ሰዎች ለምንድነው እኛን እንደ ኢትዮጵያዊ የማትቆጥሩን?›› አለ በቁጣ፤ ወዳጄ አፍሮ፣ ይቅርታ ጠይቆ፣ ወደነበረበት ወንበር ተመለሰ ‹‹ተፎገርኩ! ሱዳናዊ ወይም ናይጄሪያዊ ወይም ኬንያዊ ይሆናል ብዬ የጠረጠርኩት ሰው- የጋምቤላ ተወላጅ ሆኖ አላገኘው መሰለህ!›› አለኝ፡፡ብዙዎቻችን እንዲህ ነን፡፡ አናያቸውም፣ አንለያቸውም፣ በእንግዳ ዓይን ነው የምንቀርባቸው፤ የዚህች ሀገር ጉዳይ ግድ የሚሰጣቸው አይመስለንም፤ ስለአኗኗራቸው የጠለቀ እውቀት የለንም፤ ትምህርት ቤት፣ ታክሲ ውስጥና በየመዝናኛ ስፍራው ስናገኛቸው መንፈሳቸው ቶሎ አይዋሃደንም፡፡ ለምን? ምን ሆነን ነው ራሳችንን ያጠበብነው?!ከጥቂት ወራት በፊት፤ በፌዴሬሽን ምክር ቤት አስተባባሪነት ከመቶ ሃምሳ የማናንስ የኪነ-ጥበብ ሰዎች የኢትዮ-ሶማሌን ምድር የመርገጥ እድል አገኘን፤ ጉዞው ሳምንት የፈጀ እና ብዙ ነገሮች እንድናገናዝብ ያደረገን አይረሴ መስተንግዶ ነበር የጠበቀን፡፡የሄድንበት ሰበብ ደግሞ÷ ተወላጆቹ እኛ የኪነ-ጥበብ ሰዎችን ከስሰው ነው፡፡ ለወቀሳ፡፡ ‹አታውቁንም፣ እንደ ኢትዮጵያዊ አትቀበሉንም፣ እኛን አዲሣባ ወይም በሌሎች ከተሞች ስታገኙን ከሞቃዲሾ የመጣን ይመስላችኋል፤ የዚያድባሬ ጉዳይ የሚያሳስበን ይመስላችኋል፤ ታላቋ ሶማሌ እንድትመሰረት እንቅልፍ የምናጣ ይመስላችኋል፤ ኢትዮጵያዊነታችንን ላለመልቀቅ ስለምናደርገው ተጋድሎ አታውቁም፤ በዘፈኖቻችሁ፤ በፊልሞቻችሁና በልቦለዶቻችሁ ውስጥ የለንም፤ እናንተ ውስጥ ቦታ የለንም፤ መሬታችንን ረግጣችሁ አታውቁም፤ አርቃችሁናል› ብለው ነው ማንነታቸውን በጨረፍታም ቢሆን ያስጐበኙን፡፡እዚያ ሄደን - ያየነውና የሰማነው ልብ የሚነካ ‹ለመገንጠል ያለመፈለግ ተጋድሎ› አሁን የሚነገር አይደለም፤ ወቀሳቸውን ግን ብዙዎቻችን ተቀብለነዋል፤ በጅጅጋው ሶማሌና በሞቃዲሾው ሶማሌ መካከል ስላለው የአመለካከት ልዩነት ብዙዎቻችን ጠንቅቀን አናውቅም፤ በአንድ ሚዛን ነው የምንመዝናቸው፡፡በተለምዶ እኛ ‹ፈላሻ› የምንላቸው፤ መጤ እንግዶች ናቸው ከውጪ የፈለሱ የምንላቸው፤ እነሱ ግን ‹ፈላሻ› ሲባሉ ደስ የማይላቸው፤ ራሳቸውን ‹ቤተ እስራኤላዊ› ብለው የሚጠሩ፤ እስራኤሎች ደግሞ ‹የኢትዮጵያ አይሁዳውያን› ብለው የሚጠሯቸውን ማኅበረሰቦችንስ እንዴት ነው የምናያቸው?‹ዛጐል› የሚባል አንድ ልቦለድ መጽሐፍ አለኝ - መሪ ገፀ-ባህርዩ ቤተ-እስራኤላዊ ነው - ከልጅነቱ ጀምሮ ቡዳ - የቡዳ ዘር ተብሎ የተገለለ፣ በሃይማኖቱ የተነሣ - እንደ አናሣ፣ እንደ መጻተኛ፣ እንደ መጤ የተቆጠረ፡፡ እና ራሱን እንዲህ ይገልፀዋል ‹…እንደ ጂፕሲ ነኝ፤ ጂፕሲ መሆን ማለት የመጣበት የማይታወቅና እንኳን ደህና መጣህ የማይባል እንግዳ መሆን ማለት ነው ብሏል አሉ አንድ ምሁር፡፡ ‹ጂፕሲዎች› በየትኛውም ዓለም የተናቁ ናቸው፡፡ ሙዚቃቸውና ዳንሳቸው ብቻ ነው ተወዳጅ፡፡ የሁልጊዜ ስደተኞች ናቸው፡፡ … በጣም የተጠሉ፣ የተገፉ፣ ተረጂነት መለያቸው የሆኑ ህዝቦች ናቸው…›ምንም እንኳን ገጸ-ባህርዩ ያጋነነውን ያህል ባይሆንም፤ ቤተ-እስራኤላውያን ብዙ መገለል ደርሶባቸዋል፤ አድልዎ ተፈፅሞባቸዋል፤ መንከራተት ዕጣ-ፈንታቸው ሆኗል (ወደፊት ስለእነዚህ ሰዎች ሰፊ ነገር አስነብባችኋለሁ)ይህ ሁሉ ሀተታ ‹ኢትዮጵያ የሁላችንም አልሆነችም› ለማለት ነው፤ ገፍተንና ገፍትረን አውቀንም ይሁን ሳናውቅ ዳር ያስያዝናቸው ማኅበረሰቦች አሉ ለማለት ነው፡፡ኢትዮጵያ የሁላችንም ትሁን፤ ኢትዮጵያ ጥቂት ብሄሮች፣ ጥቂት ምሁሮችና ጥቂት ታጋዮች ኮሚቴ መስርተው የሚመሯት አገር አይደለችም፤ እኩል ይዝነብልን፤ ለጥቂቶች ሲዘንብ አይደለም ለተቀረው ማካፋት ያለበት፤ ጥቂቶች ሲጠግቡ አይደለም የተቀሩት እንደ ተመፅዋች ‹ትራፊ› በጀት ሊበጀትላቸው የሚገባው፡፡አሁንም ያልተቀበልናቸው አሉ - አናሣ ብለን፣ ሳናውቃቸው ቀርተን - መጤ ናቸው ብለን፡፡ እንግዳ ተቀባይ ስለመሆናችን እንናገራለን፤ በመስተንግዶአችንም እንኮራለን፤ ጥሩ ነው እንግዳን መቀበል ስደተኛን ማስጠጋት፡፡ እንግዳ ስንቀበል ግን ቤት ውስጥ ያለውን ዘንግተን፣ ችላ ብለንና ፆም አሳድረን መሆን የለበትም፤ ይህን ካደረግን ግብዝነት ነው፤ በግዕዝ አንድ አባባል አለ ‹ለእመ ሀሎ ርሁበ ውስተ ቤትከ እታውፅእ አፍኣ› የሚል - ‹በቤትህ ወይም በደጃፍህ የተራበ እያለ ምፅዋትህን ወደ ውጪ አታውጣ› ለማለት፡፡...በቤታችን፣ በደጃችን፣ በጓዳችን፣ በጓሮአችን ስንቶቹ ናቸው ፍቅር ተርበው÷ ክብር ተነፍገው፣ ፍትህ ተጠምተው እየኖሩ ያሉት?ል
Published on September 19, 2013 04:34
September 4, 2013
መክሊታቸውን ለቀበሩ
1እንደመድሀኒት አዋቂ ነንየየሙያችን ’ኤክስፐርቶች’።ለቤታችን አጥር ሰርተን፤ለልባችን አጥር ሰርተን፤ለዕውቀታችን አጥር ሰርተን፤ዙሪያችንን በሾህ አጥረንአልፎ ሂያጁን ተጠራጥረንከኮራጅ መሳይ ዕውቀት አሳሽምስጢር ወሳጅ የልብ ወዳጅበር ዘግተን ደጅ ቆልፈንያለን፤ እንደ መድሀኒት አዋቂ ነን!2
በተክርስቲያንም - ቤተ እስልምና
“አይተኬው ዕንቁ ፍጡር!” “አይጠጌው ጭንቂው ምሁር!”ምኑጋ ነው ዕንቁነቱበምን ታይቶ ጭንቄነቱ ካላፈራ ደቀመዝሙር?
Published on September 04, 2013 00:39
September 3, 2013
ከጥቁር ሰማይ ስር
ጥዋት ጥዋት፣ ወደ ቢሮ ለመሄድ - መታጠፊያው ጋ ሲደርስ - እተለመደ ቦታዋ ቁጭ ብላ የሚያጉተመትም በሚመስል ድምጿ ያለማቋረጥ ስታወራ ይሰማታል፡፡ የአራት ልጆች እናት የሆነችዋን የኔ ቢጤ፡፡ የእናታቸውን ያህል ባይሆንም ጎስቁለዋል፡፡ እንደ ምጣድ ማሰሻ የቀድሞ ከለሩ ያልታወቀ ከነቴራ ለብሰዋል - ከወገባቸው በላይ፡፡ ከመሃከላቸው አንዳቸውም ቃጭል አንጠልጥለው አልተወለዱም፡፡. . . በማያውቀው ቋንቋ ታወራቸዋለች፡፡ ልጆቿ አይመልሱላትም፡፡ እርስ በርሳቸው ሲጨዋወቱ በአዲስ አበባ አማርኛ ነው የሚግባቡት፡፡ እንዲህ በከንቱ ጉንጭዋን የምታለፋው በውስጡ ያደረውን ጩዋሂ መንፈስ ላለማዳመጥ ይሆን? ብሎ ያስባልጤንነቷን የማይጠራጠር የለም፡፡ አንዳንዶች ፥ ስለ ልጆቿ የወደፊት ዕጣ ፈንታ ማሰላሰል ስታበዛ ይሆን ያተሳሰብ ማዛንዋ የተዛባው? ይላሉ፡፡ ሁልጊዜ ያልተለመደ ነገር ስታደርግ ያጋጥመዋል፡፡ እጇ ላይ የተገኘን ማንኛውም ነገር ለአራት አካፋፍላ ለልጆች ታድላቸዋለች፡፡ ለራሷ የምታደርገው አይኖራትም፡፡ ከሲታ ናት ደግሞ፤ ያለ እህል ውሃ ለመኖር ሙከራ የጀመረች እስኪመስል ድረስ፡፡ ሳንቲም ተወርውሮ እግሯ ስር ያረፈ እንደሆነ ቅጭልጭልታውን ሰምታ እንኳን ቀና አትልም፡፡ ማንንም አይታይም - አገጯን ጉልበቷ ስር ደብቃ ነው፤ ቀኑን ውላ የምታመሸው፤ የምታነጋውም! መንገድ ዳር፡፡ የልጆቿ አባት ይሆን? . . . ወይስ ወደ ጎዳና ከወጣች በኋላ የተወዳጃት ጊዜያዊ ባል?! . . . ወይስ ከክፉ ሊታደጋት ተከትሏት የመጣ . . . ? ወይስ ለነፍሱ ያደረና እነዚህን ሕጻናት ታድጎ በቅዱሳን መዝገብ ስሙን ለማስጻፍ የሚተጋ ይሆን? ከሁላቸውም የምታንሰዋ ሕጻን ዕለተሞቷ የተቃረበ ገመምተኛ ነው የምትመስል፡፡ ሁለት ዓመት ይሆናታል፡፡ የምትተልቀዋ ስድስት እንቁጣጣሾች አክብራለች፡፡ ከእናቷ ጎን ፈቀቅ ሳትል ወጭ ወራጁን ታጤናለች፡፡ ከአጠገቧ አንድ ሰው ያለፈ እንደሆነ ‘ጋሽዬ ለዳቦ?’ ብላ ተለሳልሳ ትለምናለች፡፡የተሰጣትን አጠራቅማ ሃምሳ ሳንቲም ሲሞላ ዳቦ ለመግዛት ሩጫዋን ታቀጥነዋለች፡፡ ታናናሾቿም ከተደበቀችበት ክንፍ አፈትልካ እንደምትወጣ ጫጩት ከእናታቸው ጉያ ሾልከው ይከተሉዋታል፡፡የገዛችውን ዳቦ እናቷ እጅ ላይ ታኖረዋለች፡፡ እናት ዳቦውን ለአራት ታካፍለዋለች፡፡ ለራሷ የምታስቀረው የላትም፡፡ ልጆቿም እንድትበላላቸው አያባብሏትም፡፡አንዳንዴ፣ ስለ እናታቸው ምን ያስቡ ይሆን? ብሎ ያስባል፡፡ ሳይሳለማቸውና ድምጹን ሳያስደምጣቸው ማደር አይሆንለትም፣ አንጀቱ እየተንሰፈሰፈ በደስታ ይጨብጣቸዋል፡፡ እጁን ለመንካት ይሩዋሩዋጣሉ - እየተጩወጩዋሁ፡፡እናትየው ይህን ሁሉ አታይም፡፡ ቀና ብሎ የው ዓይን ማየት የሚሆንላት አይመስልም፡፡ ብታያቸው ለመደሰቷ ምክንያት መሆን ቢችል ደስ ይለዋል፡፡ ፊገግታ ፊቷ ላይ ሲጫወት ምን እንደሚመስል ማየት ያልፈለገበት ጊዜ ይኖር ይሆን?ማታ፡፡ሳንቲም ፍለጋ ኪሶቹን ደባበሰ፡፡ ድፍን አምስት ብር ተገኝታለች፡፡ ዙሪያውን ቃኘ፡፡ ያልተዘጉ ሱቆች አይታዩም፡፡ የት ይዘርዝረው?ለአራት ተዘጋጅታ የነበረች ብር ናት፡፡ ምሳ ሳይበላ ነው የዋለው፡፡ ሳይበላ ስለዋለ ነው መሰል ከተራራ ላይ እየተንከባለለ እንደሚወርድ በርሜል ሆዱ ሲያጉረመርም ይሰማዋል፡፡ ብሩን የት ይዘርዝረው?የተቻኮሉ መገደኞች በጥርጣሬ እያስተዋሉት ይተላለፋሉ፡፡ ግን ማንንም ‘ዝርዝር ከያዛችሁ ተቸገሩልኝ’ ብሎ መጠየቅን አልፈለገም፡፡“ምሳና እራት ሳልበላ ብቀር ምን ይጎድልብኛል?” ብሎ ሆዱን ሲደልል ቆየና አምስት ብሩን አወጣ፡፡ አወጣና ሌላ ጊዜ እንደሚያደርገው አጠገባቸው ጣል አድርጎ ‘ደህና እደሩ’ ማለቱን ብቻ አልፈለገውም፡፡አምስት ብሩን በእናትየው መዳፍ ላይ አኖረው፡፡ፈገግታ አላሳየችውም፡፡ አላየችውምም፡፡ ድምጿም አልተደመጠ፡፡ትልቋ ልጅ ብቻ ናት - በእጃቸው ትልቅ ነገር እንደገባ የገባት፡፡ እንደመፈንደቅም እንደመደንገጥም ብላ የተኙትን ቀሰቀሰቻቸው፡፡ ለማንቃት አልተቸገረችም፡፡ ጠባቂያቸውን ግን ተወችው፡፡ ስጋውን ለእንቅልፍ አሳልፎ ሰጥቷል፡፡ አቀማመጣቸውን ልብ ብሎ ላየ እናትየው እንስራ ትመስላለች፡፡ ሕጻናቶቿ ደግሞ እንስራው ተንሸራትቶ እንዳይሰበር ደግፈው የያዙት ጠጠሮች! . . . እናትየው እጇ ላይ የገባውን አምስት ብር ለሁለት ከፈለችው፡፡ የከፈለቻቸውን የብር ክፍልፋዮች በሚያስገርም ፍጥነት እንደገና ቀዳደደቻቸው፡፡ ሁለት ሶስት ባልሞላ ደቂቃ ውስጥ ለልጆቿ አከፋፈለቻቸው፡፡ ትልቅዬዋ ለምቦጭዋን ጥላ በእጇ የነበረውን ሳንቲም እናቷ እናት ላይ በተነችው፡፡ “ብዙ ዳቦ የሚገዛ፣ ሁልጊዜ እንዳይርበን የሚያደርግ፣ ብር ነው ኮ እንደዚያ የማይጠቅም ያደረግሽው!” አለቻት ሳግ እየናነቃት፡፡እናት የተባለችው ያልገባት ይመስል ልጇ ላይ አተኮረችባት፡፡ መፅዋቹም ትርጉሙን ባልተረዳችው አተያይ ሲያያት አገኘችው፡፡ እንደተያዩ ቆዩ፡፡ ትናንሽ ዓይኖቹ እንባን ያዘንቡ ጀመር፡፡ እንባው እየንሸራተተ - በጠይም ፊቱ ላይ መስመር እያበጀ - ወደ አፉ ደረሰ፡፡ይሄ ሲሆን አምስት ብሩን የሸረካከተችው እናት ልብ ብላ አየችው፡፡መፅዋቹ መንቀሳቀስ ጀመረ፡፡የሚንቀሳቀስ ጥላ መስሎ በዝግታ እየተጓዘ ወደ ጨለማው ሆድ ውስጥ ገባ፡፡ ቅርፁ እስኪርት ድረስ በዓይኗ ሸኘችው፡፡ ከዚያስ በኋላ . . .ሌቱን በሙሉ - በታላቅ ምሬት - ባለተለመደ አጩዋጩዋህ ስትንሰቀሰቅ አደረች፡፡ አምስት ብሩን
ያለ አገልግሎት ስላስቀረችው ሊሆን ይችላል፡፡ ያቺ ብር ርሃቧን ልታስወግድበት ትችል እንደነበር ተገንዝባ ይሆናል፡፡ ወይም የዚያን መፅዋች እንባ ስታይ አንድ ነገር እንዲታወሳት ምክንያት ሆኖ ይሆናል፡፡ለምን እንዲህ እንዳደረገች
የጠየቃት አልነበረም
Published on September 03, 2013 23:42
August 29, 2013
በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን አርሂቡ ፕሮግራም ላይ በቀረብኩበት ወቅት
Published on August 29, 2013 01:48
August 28, 2013
ያልተቀበልናቸው…(ክፍል 1)
ያልተቀበልናቸው…(ክፍል 1)
…ኢትዮጵያ ውስጥ እያሉ፤ ኢትዮጵያዊ እየሆኑ፤ እንደውጭ ዜጋ የምንቆጥራቸው አሉ፤ እንደ ውጭ ዜጋ ባንቆጥራቸውም ‹የእኛ ናቸው› ብለን አምነን ለመቀበል የምንቸገርባቸው አሉ - ከእነዚህ ብሄሮች ወይም ማህበረሰቦች ጋር አንድ ማዕድ አንቀርብም፤ ከብቶቻቸው ከከብቶቻችን ጋር አይውሉም፤ በጋብቻ ተዛምደን አጥንታቸው ከአጥንታችን ደማቸው ከደማችን ጋር አይዋሃድም፤ አልተቀበልናቸውም -ልክ እንደ መጻተኛ - ልክ እንደ ባይተዋር - ልክ እንደ ድንገተኛ እንግዳ - የሚታዩ ሆነዋል፡፡ ሀገሪቷ ከህጋዊ ባሏ ያልወለደቻቸው ይመስል ሳቅና ለቅሶዋን ከተቀሩት ልጆቿ እኩል የማይካፈሉ የሚመስለን፤ ውለታ የማያኖሩላትና ብድር የማይከፍሉላት የሚመስለን፡፡ ሳናውቃቸው፣ ሳንቀርባቸው፣ ሳንጠይቃቸው የሚያልፍ - ጥላ መስለው፣ ጥላ ለብሰው፡፡
በተለያየ ጊዜ የጻፍኳቸው አንዳንድ የፈጠራ ስራዎቼ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ፤ እነዚህን - የተገፉና የተረሱ የመሰሉኝን ማህበረሰቦችን የሚዳስሱ ሆነው አግኝቼያቸዋለሁ፤ እነዚህ ማህበረሰቦች ብዙዎቹ ሀበሾች አይደሉም፤ ለሀበሾች የሚሰጠውን የክብርና የጌትነት ሹመት የታደሉ አይደሉም፤ በገዛ ቤታቸው እንግዶች ናቸው፤ በገዛ አገራቸው እንደ ቀላዋጭ የተቆጠሩ ናቸው፤ እንዲህ አይነቱ አካሄድ ሊበቃ ይገባዋል ባዮችና የ‹ያ ትውልድ› አባላት ‹‹የኢትዮጵያ ብሄራዊ ስሜት÷ በአብላጫው ከሀበሻ ህዝብ ጋር ነበር የሚዛመደው፡፡ ሀበሻነት ደግሞ ከትግርኛና አማርኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች በመለስ የተቀረውን የኢትዮጵያን ሕዝብ አያካትትም›› ብለው ነው የብሄር ጥያቄ እንዲነሳ ያደረጉት፡፡ጥያቄው የተነሳበትን 50ኛ ዓመት (የወርቅ ኢዮቤል በዓል) እናከብር እንደሆን ነው እንጂ፤ ያለፉት መንግስታት ለጥያቄው መልስ የሚመስል መልስ ሰጡ ወይም ለመስጠት ሞከሩ እንጂ፤ የጠያቂዎቹ ልቦና በመፍትሄ እንዲረካ አላደረጉም፡፡ እንዲህ አብራራዋለሁ፡፡‹አናሳ› ኢትዮጵያውያን የሚባሉ ነበሩ (?) ቃሉ ደስ አይልም፤ ‹አናሳ› መባል ደስ አይልም፤ አናሳ ማለት ራስንም ያሳንሳል - ተናጋሪውን፡፡ አናሳነት ትንሽነት ነው፤ ትንሽነት ዓይነ-ገብ አለመሆን ነው፤ ቃሉን በስፋት የተጠቀመበት ደግሞ ኢህአዴግ ነው፤ ከኢህአዴግ በፊት አናሳ ብሄሮች ሲል የሰማሁትም ሆነ ያነበብኩለት ኢትዮጵያዊ መንግስት የለም፤ ቃሉን ይጠቀም የነበረው የቁጥራቸውን ማነስ ለመግለጽ ነበር ብዬ እገምታለሁ፡፡የሆነው ሆኖ አናሳ መባል የሚያሳምማቸው በዝተው ነው መሰለኝ -በየጠረፉ፣ በየጥጋጥጉ፣ በየጉራንጉሩ ያሉ ‹ዝነኛ› ያልሆኑ ብሄሮች - አናሣ አንባል ብለው መንግስትም ሚዲያውም ቃሉን አይጠቀምበት ጀምሯል፡፡በአደባባይ አንናገረው እንጂ ሁላችንም ጭንቅላት ውስጥ አናሳ የምንላቸው አሉ፤ አናሳ ስል በህሊናችን ውስጥ ቦታ ያልሰጠናቸውና የሚገባቸውን ሥፍራ ያልለቀቅንላቸውን ማለቴ እንጂ ቀጥዬ የምጠቅሳቸውን ጐሣዎችና ማህበረሰቦችን ዋጋ ለመንፈግ የምጠቀምበት አይደለም፡፡እንደምታውቁት ኢትዮጵያ ውስጥ በትክክል ካልተነገሩን መረጃዎች መካከል አንዱ የብሄር ብሄረሰቦቻችን ቁጥር ነው፤ ‹ከ80 በላይ› ወይም ‹የበርካታ ብሄረሰቦች ሀገር የሆነችዋ ኢትዮጵያ…› ነው የሚሉት ሹማምንቱ፣ ግና ከ80 ወይም ከ85 በላይ ማለት ምንድነው? ማነው እርግጠኛ የሆነውን ቁጥር ሊነግረን የሚገባው?ከጥቂት ዓመታት በፊት ወደ ደቡብ ኦሞ ሄጄ ነበር- ጂንካ፡፡ ጂንካ ከተማ ውስጥ አንድ ‹ታፔላ› ተሰቅሏል፤ ‹ታፔላ›ው በደቡብ ኦሞ ስር ያሉ ብሄሮችን ስም ይዘረዝራል፤ አስራ ሁለት ናቸው፤ ሀመርን ጨምሮ! ይህንን መረጃ ይዤ፤ እምፈልገውን መረጃ ለማግኘት ስሄድ ግን፤ የጂንካ ባህልና ቱሪዝም አንድ ‹ኤክስፐርት› ብሄሮቹ አስራ ስድስት መሆናቸውን ነገረኝ -‹‹ታፔላው ከተሰቀለ በኋላ ነው አራቱ ብሄሮች የተገኙት?›› ብዬ ጠየቅኩ፤ ‹‹አዎን! …ወደፊትም ይገኝ ይሆናል!›› ነበር ምላሹ፡፡በቅርቡ ለሕትመት የበቃው የአንዱዓለም አባተ (የዐፀደ ልጅ) ‹መኤኒት› ልቦለድ ላይም ያስደመመኝ ነገር አግኝቻለሁ፤ ልቦለዱ ለዘመናት የተገፉ፣ የተረሱና የአናሳነት ‹ማዕረግ› የተሰጣቸውን የ‹መኤኒት› ብሄረሰቦችን የሚያሳይ ነው- ፍቅረማርቆስ ደስታ ‹ከቡስካ በስተጀርባ› ብሎ ሀመሮችን እንዳሳየን፣ ዳንኤል ግዛው ጽፎት መዝሙር ፈንቴ የተረጐመው ‹አፍሪካዊው ልዑል› ደግሞ መንጃ፣ በና፣ ኩሌዎችንም እንዳስነበበን፣ ለማ ፈይሣ ‹ጉራጌው›፣ ዳኜ አሰፋ ‹ኬርታ› ብሎ የጉራጌዎችን ማኅበራዊ አኗኗር እንዳመለከቱን… መሆኑ ነው፡፡‹መኤኒት› ውስጥ አንዲት ቀበሌ አለች፤ ቀበሌዋ ያርጣ ትባላለች፤ ‹በሁለት ሺህ ዓ.ም ነው የተገኘችው፤ ከዚያ በፊት በዚያ አካባቢ ሰው መኖሩ አይታወቅም ነበር› ይላል ልቦለዱ ‹…ምንም አይነት የትራንስፖርትና የመገናኛ አውታር የለም፡፡ አሁን እንኳን በእግር ሃያ ሶስት ሰዓት ተጉዞ ነው እዚያ የሚደረሰው፡፡ በርካታ ጉብታና ሸለቆ ማለፍ፣ እልም ያለ በረሃን ማቋረጥ ያስፈልጋል› (ገፅ 109)ነገሩ በቸልታ የሚታለፍ መረጃ አይደለም፤ እውነት ከሆነ ከመገረምም አልፎ ያስደነግጣል ‹ያርጣ› ቀበሌ ከመገኘቷ በፊት ማን ነበር አስተዳዳሪዋ? መንግስት እንዴት እንደማዕድንና እንደ ነዳጅ ድንገት አንድ ቀቀበሌ አግኝቻለሁ ይላል? የት ነበሩ? ከከተማው ሃያ ሶስት ሰዓታት በእግር ተጉዞ የሚደረስባቸው እነዚህ ማኅበረሰቦች በትክክል ‹መኤኒት› ናቸው? አኗኗራቸው የእነዚህን የመሰለ ነው ወይስ ራሳቸውን የቻሉ የአንድ ብሄር አባላት? ብሄር ከሆኑ ስማቸው ማን ነው? ተቆጥረዋል ወይ? - የሚል ጥያቄ መጥቶብኛል ልቦለዱን ሳነብ፡፡አብዛኛው ብሄር የሚንቀውና የሚርቀው ሌላ ‹ብሄር› አለው፤ ሌላ ማኅበረሰብ አለው፤ እነዚህ ‹መገለልና አድልዎ!› የሚደርስባቸውና እንደ አናሳ የሚቆጠሩ ሕዝቦች - ከተለመደው የአኗኗር ፈሊጥ ወጣ ያሉና ያፈነገጡ በመሆናቸው ተከባሪ አይደሉም፡፡ከዚህ በፊት ‹ኬርሻዶ› በሚለው ኢ-ልቦለድ መጽሐፌ ላይ እንደገለጽኩት፤ ሰባት ቤት ጉራጌ ብትሄዱ ፉጋዎችን ታገኛላችሁ፤ ‹ፉጋዎች በአካባቢው ተወላጆች ዘንድ የተናቁ ናቸው ይባላል፡፡ ቡና እንዲጠጡ ሲጋበዙ እንኳን የራሳቸውን ስኒ ነው ይዘው የሚመጡት፡፡ ስኒያቸው ከሌሎች ስኒዎች ጋር አይደባለቅም፡፡ እነሱ በጠጡበት ስኒ ቡና የሚጠጣ የለም፡፡ እነሱ ቡና ካፈሉ የሚጋብዙትም ሆነ የሚጋበዝላቸው የለም፡፡ ‹ደርግ ነው ከሰው እኩል ያደረገን› ይላሉ፡፡ እኩል ነን ብለው ግን አያምኑም ደርግ መጥቶ፣ አብዮት ፈንድቶ የማያውቁትን ዓለም አሳያቸው ‹ከማንም አታንሱም ከማንም አትበልጡም› አለና፤ ከጓሮ አውጥቶ እደጅ አስቀምጦ አስደነገጣቸው፤ ድንጋጤው አሁንም ቢሆን አልፎ አልፎ በልጆቻቸውና በልጅ ልጆቻቸው ላይ ተባዝቶ አየዋለሁ…›ስማቸው ‹ፉጋ› አይሁን እንጂ እንደነዚህ ዓይነት ማኅበረሰቦች በየገጠሩ፣ በየብሄሩ አሉ፡፡ - ደርግ ጭቁን ብሄረሰቦች ነበር የሚላቸው፤ እኔ እንደሚገባኝ - ያነበብኳቸው መጽሐፍትም እንደሚጠቁመኝ ደርግ - ኢትዮጵያ የሀበሾች ብቻ እንዳልሆነች ለማመንና ለማሳመን ራሱን አዘጋጅቶ ወታደራዊ ሀይል ተጠቅሞም ነበር፤ ስማቸው ተሰምቶ የማይታወቁ ብሄረሰቦች የት መጣነታቸው እንዲታወቅና የጋብቻና የፍርድ አሰጣጥ ሂደታቸው ምን እንደሚመስል ይዘገብበት ዘንድ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ የባህል ዓምድ ከፍቶ ነበር፤ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የፎክሎር ትምህርት እንዲሰጥና እያንዳንዱ ባህል ማንነቱ እንዲጠና፣ ትውፊታዊ በዐሉ እንዲመረመር የእውቀት ገበታ አዘርግቶ ነበር፡፡ መስከረም ሁለት ሲመጣ ‹ለዚህ ያበቃን አብዮቱ ነው› ለማለት አለቆቻቸው ፊት የምርቶቻቸውን ውጤት ይዘው፤ በባህላዊ አልባሶቻቸው አጊጠው በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው የምስጋና መብዓ ያቀርቡ ነበር፤ ያም ሆኖ ‹ምሉዕ› አልነበረም - በአፄ ኃይለሥላሴ ዘመን ከነበረው የተሻለ ትኩረት ተሰጣቸው እንጂ!
Published on August 28, 2013 01:05
August 27, 2013
ሲጨልም
ወደ ሰባዎቹ የሚጠጉ የሚመስሉ አንድ አረጋዊ “ልጄ” አሉት አስተናጋጁን፡፡ “የወሰድኩትን መድኃኒት ይዤብህ መጣሁ፣ እባክህን የሰጠኸኝን ወስደህ . . .”አላስጨርሳቸውም፡፡ ግርግዳው ላይ ወደተለጠፈው ጽሑፍ አመለከታቸው፡፡ ‘የተሸጠ መድኃኒት አይመለስም አረጋዊው’በለሰለሱ ቃላት መማፀን ያዙ፡፡“ሰውዬ ዞር በል! ስራ ልስራበት! ለእንቶ ፈንቶ ጉዳይ የማባክነው ጊዜ የለኝም. . .” አለ ቁጣው እየተወለደ፡፡ “ዛሬ በዚህ ሰውዬ እንድጨቀጨቅ ተፈርዶብኛል ልበል?”“እባክህን ልጄ አሳፋሪ ነገር ደርሶብኝ ነው ዘመድና ዕድር የለለኝ በመሆኑ እንጂ . . . ” አሉ ትሁት በሆነች ፈገግታ ሊያባብሉት እየሞከሩ፡፡“ቅናሽ ዋጋ ብትከፍለኝም . . .”“ይሄ ሰውዬ ነካ ያረገዋል ልበል?” አለና ሌሎች መድኃኒት ገዥዎችን ያስተናግድ ገባ፡፡ “ከያዙ አይለቁ”
“ድህነት ቢፈትነኝ ነው ልጄ” አለ¸ያደፈና የነተበ ነጠላቸውን እያሳዩት፡፡ ነጠላው ከሰውነታቸው በከፋ ሁኔታ ያረጀውን ኮታቸውን ደብቆላቸዋል፡፡“አቅሜ የደከመ ባይሆን ኖሮ . . . ” ጫማ ካገኘ የከረመ እግራቸውን እያዩ፡፡ አንዲት ተስተናጋጅ “አልመልስም ካለ አልመልስም ነው፡፡ ለምንድነው የሚነዘንዙት?” አለች በሚነጫነጭ ድምጽ “ይሄኮ ፋርማሲ እንጂ አዛውንቶች የሚጦሩበት የድኩማን መርጃ ድርጅት አይደለም”አነጋገሯን ያልወደደው የሚመስል ሌላኛው ጎልማሳ ደግሞ “መድኃኒቱን ሙሉ በሙሉ የገዙት ከዚሁ መደብር ነው?” የሚል ጥያቄ አመጣ፡፡“አዎ ዶክተሩ ፅፎ በሰጠኝ መሠረት”“ምን ያሕል ፈጀብዎት?”“ሰባ ሁለት ብር ከሰማኒያ አምስት ሳንቲም፡፡ መድኃኒቱን ወስደው ግማሹን እንኳን ቢሰጡኝ ምን አለበት?” አሉ በሃዘኔታ፤ “የሁለታችንንም የጋብቻ ቀለበት አስይዤ ነው ከማምነው ሰው የተበደርኩት”“መድኃኒቱን ለምን መመለስ ፈለጉ?” ዘንቢል ያንጠለጠሉ ያንዲት ምስኪን እናት ጥያቄ፡፡በዚህ ጊዜ አስተናጋጁ ጣልቃ ገባ፡፡ “ባህላዊ ሕክምና ብትከታተል ኪስ እንደማታራቁት ገብቷቸው ይሆናላ!ወይ ፀበል ሊያጠምቋት! ወይ . . .”“ኧይ ልጄ! ጉዳዩን ብታውቀው ኖሮ ያፌዝክበት ምላስህን ታፍርበት ነበር . . .” አሉ እንባ እየተናነቃቸው፡፡ “መድኃኒቱን ምን ላድርገው? ልዋጠው ወይስ ሽንት ቤት ልጨምረው?”“ለባለቤቴ ነው የምገዛላት ብለው አልነበር? በጠና ታማብኛለች የእድሜዬ ጀምበር እየጠለቀ ባበት ሰዓት ለእህል ያላነሱና ለትምህርት ያልደረሱ ሦስት ልጆች በትናብኝ እንዳትሄድ ፀልይልኝ ብለውኝ አልነበር?”“ማለቱንስ ብዬህ ነበር ልጄ! . . . ብዬ ነበር”“እና ሩብ ሰዓት ያህል እንኳን ሳይቆዩ ሃሳብዎን አስሰርዞ የገዙትን መድኃኒት የሚያስመልስ ምን ተአምር ተፈጠረ?! ቅድም የማይመለከተኝን ነገር ሲዘላብዱልኝ ነበር እኮ” አረጋዊው አንገታቸውን ደፉ፡፡ “እኮ ምን ቢፈጠር ነው . . . ?”“ቤቴ ሳልደርስ ነው አንተ ዘንድ የመጣሁት”“ለምን?” የሌሎቹ ጥያቄ፡፡“ሰፈርተኞቼ ደጄ ላይ ሲጯጯሁ አየሁ፡፡ ባቤቴን በህይወቷ ልደርስላት አልቻልኩም!” አሉ አረጋዊው ድምጻቸው እየሻከረ፡፡ እንባቸው እየወረደ፡፡ በመድኃኒት ሻጩ ፊት ላይ ፀፀት ድንጋጤ እየታየ ድፍን መቶ ብር አውጥቶ በሻካራ እጆቻቸው ላይ አኖረው፡፡ ሌሎቹም ኪሶቻቸውን ይፈታትሹ ጀምር፡፡“ይባርካችሁ ልጆቼ! ከፈን መግዣ ስላልነበረኝ እንጂ . . . ” አንባ ተናነቃቸው፡፡መንሰቅሰቃቸውን እየቀጠሉ ወጡ፡፡ ፀጥታ!
Published on August 27, 2013 05:31
August 24, 2013
ብቻነት
ብቻነት ልቤ ውስጥ ክረምት ገባ የሀዘን ውሽንፍርየብቻነት ዶፍገላዬን አራሰው ወየው!ልቤን!ልቤን!!ልቤን!!!ነፍሴ ጎርፍ አትወድምነፍሴ ውርጭ አትለምድምጭጋግ ይጨንቀኛልብርሃን ይርበኛል…ሰው የማታ ራቴሰው የምኞት ጓዜማን ይሆን ሳምራዊማን ይሆን ቅን ወዳድእኔ ነኝ ባይ ማነውየእግዜር አምባሳደርፀሃይን ሰርቆልኝጨረቃዋን ጭምርበልቡ ሙዳይ ውስጥልቤን የሚያሳድር፡፡
Published on August 24, 2013 07:04
ሰው ለሰው
አስናቀ- ‹ተወዳጁ› ሰይጣን
አበበ ባልቻ (አርቲስት) ‹ሰው ለሰው› የተሰኘውን ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማ ዝነኛ እንዲሆን አድርጐታል ብዬ አምናለሁ፤ ‹ሰው ለሰው› ድራማ ከፍ ያለቦታ እንዲሰጠው አበበ ባልቻ ትልቅ ሚና ተጫውቷል ብዬም አምናለሁ፤ ረቡዕ በመጣ ቁጥር፤ መጥቶም በመሸ ቁጥር ሰዎች ማወቅ ከሚያጓጓቸው ነገሮች መካከል አንዱ ‹አስናቀ እንዴት እንደሰነበተ› መረጃ መለዋወጥ ሆኗል!‹ሰው ለሰው› ውስጥ ያሉ ገጸ-ባህርያትና ድራማውን በመድረስ፣ በማዘጋጀት፣ በመተወንና ሙያዊ ድጋፍ በማድረግ እየተባበሩ ያሉ ሙያተኞች ስማቸውን በልባችን ውስጥ ማስፃፍ ችለዋል፤ በክብር እንግድነት የሚፈለጉባቸው መድረኮችም ጨምረዋል፤ በአጠቃላይ የ‹ሰው ለሰው›› ሰዎች የብዙዎቻችን ቤተኞች ሆነዋል፡፡ ይኼ መታደል ነው!! ግና ደራሲዎቹ (በተለይ ሰለሞን ዓለሙና መስፍን ጌታቸው) በየመጽሔቱ ስለዚህ ተከታታይ ድራማ በሚሰጡት ቃለ መጠይቅ ተባብሮ፣ ተከባብሮና የሚያጋጥሙ ችግሮችን በብልሃት እንዴት እንደሚወጡት ብናነብላቸውም፤ ድራማው ሊጠናቀቅ እየተቃረበ መሆኑንና ከዓመት በላይ እንደማይቆይ የሰጡትን መረጃ ልብ ብንለውም፤ እንደ ቴሌቪዥን ድራማው ተከታታዮች፤ እኔንና ጓደኞቼን ሲያሳስቡ የቆዩ ሶስት ነጥቦች አሉ፤ እነዚህ ነጥቦች ከወዲሁ ማረሚያ ካልተበጀላቸው፤ ማቃኛ ካልተደረገባቸው አንዳንድ ተመልካቾችን ድንዛዜ ውስጥ ሊከቱ ይችላሉ የሚል እምነት አለኝ፡፡‹ሰው ለሰው› ውስጥ ያሉ ገጸ-ባህሪያትን ወክለው በመጫወት ብዙዎቹ የሚደነቁ ቢሆንም፤ ገጸ ባህርያቱን በመፍጠር በኩል ግን ደራሲዎች ልብ ያላሏቸው ወይም ችላ ብለው የናቋቸው ወይም በማጠቃለያ ክፍሉ ትኩረት ሰጥተን እንመለስባቸዋለን ብለው እስካሁን በቅጡ ሲዳስሷቸው ያላየናቸው ነጥቦች አሉ፤ እነሱም አንድ በድራማው ውስጥ ሴቶችን ደካማ አድርጐ መሳል፤ ሁለት፣ ተመልካቹ እንደ አርአያ የሚወስዳቸው ቤተሰቦች አለመኖር፤ ሦስት፣ ‹ሰይጣን› የሆነውን ገጸባህርይ አጀግኖ አሳዳጅ ፖሊሱን አኮስምኖ የማቅረብ ሁኔታ…
በ‹ሰው ለሰው› ድራማ ውስጥ ያሉ ሴት ገፀ-ባህርያትን ልብ ብዬ እንዳያቸው ያደረገኝ ወዳጄ ዳዊት ንጉሱ ረታ ነው፤ ‹ሴቶቹን እዩዋቸው፤ ወጣቶቹም በእድሜ የገፉትም በቸገራቸው ጊዜ መፍትሄ ከማመንጨት ይልቅ መደናበርና መደናገር ይታይባቸዋል፤ በቀላሉ ተሸናፊዎች ናቸው፤ ምንዱባን! ለሀዘናቸው መጠጊያና መጠለያ እንዲሆን የሚመርጡት ወንድን ነው፡፡አይጠይቁም፣ አይራቀቁም፣ በወሬ ይሰበራሉ፤ ወንዶችን ያምናሉ፤ በቀላሉ ለፍቅር ይንበረከካሉ፤ በቀላሉ በስጦታ ይደለላሉ፤ በቀላሉ የንዋይ ሎሌ ይሆናሉ፤ በቀላሉ ቀላል ይሆናሉ- ተመሳሳይነት ይታይባቸዋል፤ ይሄ የደራሲዎቹ ችግር ነው፤ አብዛኞቹን ሴት ገጸ-ባህርያት ለምንድነው አንድን ነገር በጥልቀት ከመመርመር ይልቅ፤ ድንገት ወደ ህይወታቸው ጠልቆና ዘልቆ የገባ ወንድ ወደፈለገበት አቅጣጫ የሚያሽከረክራቸው?›…ሌላው የሚያሳስበን የገጸ-ባህርያቱ ቤተሰባዊ ህይወት ነው፤ ‹ሰው ለሰው› የተለያዩ ቤተሰቦች ከልጆቻቸው ጋር የሚያጋጥሟቸውን ፈተናዎች ለማሳየት የተመቻቸ ነው፤ ደራሲዎቹም ይህንን ለማዋቀር በብዙ እንደደከሙበት ያስታውቃል፤ ድርሰቱ ብዙ ቤት ገብቶ ይወጣል! ይህ ብዙ ጉድ አይቶ የመውጣቱ ነገር ይበል የሚያሰኝ ቢሆንም፤ በቤተሰቦቹ በኩል የሚነገሩን እውነቶች ግን ድካም ይታይባቸዋል፡፡በ‹ሰው ለሰው› ውስጥ ያሉ ቤተሰቦች ‹አብሬያቸው በኖርኩ!› የሚያስብሉ አይደሉም፤ እያንዳንዱ ቤት ውስጥ ጋጠ-ወጦች አሉ፤ ተበደልኩ ባይ አኩራፊዎች አሉ፤ ተስማምተው በፍቅር ከመኖር ይልቅ ወደ እርቅ የሚወስደውን መንገድ ከመያዝ ይልቅ፤ ወጣት ገፀ-ባህርያቱ ወላጆቻቸውን የሚያንጓጥጡ ይሆናሉ፤ አፈንግጠው የሚወጡ ይሆናሉ- ደራሲዎቹ በአንድ ወጣት ላይ አንድ ችግር ሲከሰት ወጣቱ ችግሩን ለማስወገድ የመረጠው ሀሳብ ተቀባይነት ሳያገኝ ሲቀር ሻንጣ አንጠልጥሎ መውጣት ወይም አገር ለቅቆ መጥፋትን መፍትሄ ያደርጉታል፡፡ በድራማው ውስጥ አንድ ገፀ-ባህርይ እንዲህ ያደርግ ይሆናል፤ ሁሉም ወጣቶች ከቤታቸው ራሳቸውን አባርረው ለወላጆች ጭንቀት መንስኤ የሚሆኑበት ምክንያት ግን አይታየንም፤ እንዴት እንዲህ ተወዳጅ በሆነ-አእምሮን ሰቅዞ በሚይዝ ተከታታይ ድራማ- እንደ ‹አርአያ› የሚቆጠር ግለሰብ ወይም ቤተሰብ ይጠፋዋል? የሚል ጥያቄ ተወልዶብናል፡፡ (ባርችን፣ የመዲን፣ የሶስናን፣ የፍሬዘር እህትን፣ የአስናቀን ልጅ ልብ ይሏል?)ሶስተኛው ነጥብ የአስናቀ ጉዳይ ነው፤ ስጀምር እንደተናገርኩት ‹ሰው ለሰው› ያለ አስናቀ ንብ የሌለው ቀፎ ነው፡፡አበበ ባልቻ ወክሎት የሚጫወተውን ገጸ-ባህርይ መጀመሪያ ዝናህ ብዙ እንዲጫወተው ታጭቶ እንደነበረ፤ ዝንናህ ብዙ ኢቲቪ ባደረገለት ቃለ መጠይቅ ገልጾ ነበር፤ ‹…ክፉ ገፀ-ባህርይ ወክዬ መጫወት ስለማልፈልግ ተውኩት! ነበር› ያለው፤ መልሱ አስቂኝ ነበር፤ አንድ አርቲስት ለትወና ሲፈለግ እኩይና ሰናይ ገፀ-ባህርያትን አማርጦ ከሰራ ምኑን የሙያው ቤተሰብ ሆነ?የሆነው ሆኖ፤ አበበ ባልቻ ‹አስናቀ›ን ተረከበው፤ እንኳንም ተረከበው!…አስናቀ የድራማው ምሰሶ ነው፤ ምሰሶው ከወደቀ ድራማው የታነፀበት ቤት ይደረመሳል፤ ራሱን ችሎ መቆም አይችልም፤ እስካሁን እንዳየነው አስናቀ ብርቱ የተባሉትን በክንዶቹ ይዞ፣ ሃይለኞችን በመዳፉ ጨፍልቆ ‹ነብር አየኝ በል› የሚያስብል ነው፡፡አበበ ባልቻ በየሄደበት የክብር ወንበር እንዲለቀቅለት ያደረገ፣ በየደረሰበት ወፍራም ጭብጨባና ሞቅ ያለ ፈገግታ እንዲቸረው ያደረገ ይኼ አስናቀ የተባለው ገፀ-ባህርይ፤ አሁን አሁን ግን ያሳስበን ጀምሯል፡፡ክፉ ገፀ-ባህርይ በዚህ ልክ መወደዱ አይደለም ያሳሰበን፤ ለምን ኢያጐን ወክሎ እንደተጫወተው ገጸ-ባህርይ ለምን መድረክ ላይ ጫማ አልተወረወረበትም፤ ለምን ሽጉጥ አልተተኮሰበትም? ማለታችንም አይደለም-ደራሲዎቹ ገፀባህርዩን ሲቀርፁ ‹የቆጡን አወርድ ብለው የብብታቸውን እየጣሉ ነው›፤ ተወዳጅ የሆነ ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማ መጻፋቸውንና ለተመልካች አሽሞንሙነው ማቅረባቸውን እንጂ በታዳሚው ህሊና ውስጥ፤ በተለይ በታናናሾቻችን ልቦና ውስጥ የተሳሳተ መልዕክት ማስቀመጣቸውን ልብ ያሉት አይመስልም፡፡ በአስናቀ ውስጥ ራሳቸውን እየፈለጉ ያሉ፣ እሱን መስለው መኖር የሚመርጡ፣ በአቋራጭ የመክበርን ጥበብ የሚኮርጁ- ገንዘብ ሊገዛው የማይችል ነገር እንደሌለ የሚያምኑ፣ ወንጀል ቢሰራ እንኳን ገንዘብ ካለው፣ ሃይል ካለው አንድም መርማሪ ፖሊስ አሳድዶ እንደማይዘው ይሰማው የጀመረ ተመልካች እየበዛ ነው፡፡አስናቀን ወደን ፈለጉን ለመከተል ታዳሚ እንድንሆን አስበው ደራሲዎቹ እንዳልጻፉት አምናለሁ፤ ገፀ-ባህርይው ከቁጥጥራቸው ውጪ እየሆነ እና አሸናፊ እየሆነ እየፈተናቸው ያለ ይመስለኛል-በሚዲያው እንዲህ አይነት ነገር መነገር አለበት ብለን አናምንም፤ ታናናሾቻችሁን ጠይቁ፤ በድራማው ውስጥ አስናቀ ነው ተፅዕኖ አሳዳሪ፤ አስናቀ ነው የሚያስቀና ኑሮ እየኖረ ያለው፡፡ይህን አይቶ ያደገ ሰው፤ ሃይለኝነትን፣ ሌብነትን፣ አማጋጭነትን፣ መሰሪነትን፣ በአቋራጭ መክበርን፣ በገንዘብ ብዛት ሰው መግዛትን ከአስናቀ የተማረ ሰው ነገ ለቁጥጥር አይቸግርም ወይ? እንላለን፤ አይደለም እንዲህ ስጋ ለብሶ ነፍስ ዘርቶ በየሳምንቱ ቤታችን የገባ ገፀ-ባህርይ ይቅርና በተረትና በታሪክ ውስጥ የምናገኛቸው ባለታሪኮች ታናናሾቻችንንም እኩዮቻችንንም የመቅረጽ አቅም አላቸው፤ በተሳሳተ መንገድ ገፀባህርይውን የሚኮርጁት እንዳይኖሩ፤ የአስናቀ የሚያስጐመጅና የማን ያዘኛል ኑሮ፣ ትኩረት ሊደረግበት ይገባል- መርማሪው ፖሊስ ምን እያደረገ ነው? እስከመቼ ድረስ ነው የሚያባርር ግን ወንጀለኛን የማይይዝ ባለሞያ ተደርጐ የሚተረበው? የፍሬዘርን ታላቅነት፣ አርቆ አስተዋይነት፣ እንደ አስናቀ ያለብርቱ ጨካኝን በቁጥጥር ስር ሲያውለው የምናየው መቼ ነው? ቀኑ አልራቀም? (ኖህ የሚባል አንድ ታዳጊ ልጅ አለ፤ መዋዕለ ህፃናት ሄዶ ከእኩያው ተጣልቶ መጣ፤ ተሸንፎ ተደብድቦ ነው የገባው - ምንሆንክ? ልጄን ምናን አገኘብኝ አለች ደንግጣ፤ ልጇን ይዛ ወደመዋዕ ለህፃናቱ ገባች፤ የደበደበኝ አስናቀ ነው አለ ለዳይሬክተሩ፤ የሚገርመው አስናቀ ግቢው ውስጥ ዝነኛ ነው፤ በአጃቢ ነው የሚንቀሳቀሰው፤ የማንንም ዕቃ ነጥቆ ቢወስድ የሚገዳደረው የለም፤ እኔ የሰው ለሰው አስናቀ ነኝ ብሏቸዋል- መጠሪያ ስሙን ቀይሮ፡፡ ይህ ታዳጊ ልጅ አቀማመጡም አነጋገሩም እንደ አስናቀ ነው…)ደራሲዎቹ ‹ሳቢዶ ሜቶዶሎጂ› በተባለው የአፃፃፍ ስልት፤ ታሪካቸውን እያዋቀሩ፣ ገፀ-ባህርያቱን እየቀረፁ ያለ ይመስለኛል፤ የአፃፃፍ ስልቱ በሌላው ዓለምም የተለመደ ነው፤ እንደ አቤል ቅን፣ ታዛዥና ንፁህ የሆነ አንድ ሰው፤ በተቃራኒው ደግሞ እንደ ቃኤል ቀናተኛና እምቢተኛ የሆነ ሌላ ገፀባህርይ፤ ክፉም ደግም ያልሆነ ሌላ ገፀ-ባህርይ ተቀርፆ፤ እነዚህን ምሰሶ አድርጐ ረብ ያለው ጭብጥ ማስተላለፍ አንዱ መለያው ነው፡፡ በዚህ የአፃፃፍ መንገድ ፓፑሌሽን ሚዲያ ሴንተር ‹የቀን ቅኝት›ና ሌሎች ተከታታይ የሬዲዮ ድራማዎችን አቅርቧል፤ ከደራሲዎቹ አንዱ መስፍን ጌታቸው ነበር፡፡መስፍንም ሆነ ሰለሞን ከዚህ ቀደም ለህዝብ ባቀረቧቸው ፊልሞች (ዙምራንና አንድ እድልን ልብ ይሏል) ማስተላለፍ የፈለጓቸው መልእክቶች ማለፊያ ነበሩ፡፡እዚህ ‹ሰው ለሰው› በተሰኘው ድራማቸው ውስጥ ግን ምንም ሳይሉ፣ ምንም ሳይናገሩበትና አንዳች መልእክት ሳያስተላልፉበት ድራማው እንዳይጠናቀቅ እሰጋለሁ፤ እስካሁን ድረስ ደራሲዎቹ የተመልካችን ቀልብ የመግዛት አቅማቸውን አሳይተውበታል፤ መሰልቸትን ለማስወገድ የተለያዩ ዘዴዎችን ቀይሰዋል፤ ገነት ንጋቱ ወክላ የምትጫወተው ገፀ-ባህርይ የተጋነነ እና ከአንዲት ኢትዮጵያዊት እናት የማይጠበቅቅ ቢሆንም፣ የት እንደገቡ ያልታወቁና ድንገት ብቅ ብለው ስቀው ወይም አስለቅሰው በእንጭጩ የሚቀጩ ቤተሰቦች ታሪካቸው ተድበስብሶ ቢያልፍም፤ ከንፁሃንና ከትጉሃን ይልቅ መሰሪዎች በተደላደለ ሁኔታ በምቹ ፍራሽ ሲንፈላሰሱ ብናይም፤ ሴቶቹ አልቃሾችና ተልከስካሾች ተደርገው ቢቀረፁም፤ ምነው እሱን ባደረገኝ፣ የእነሱ ባደረገኝ የሚያስብሉ መንፈሳዊ ቅናት የሚያሳድሩ ጠንካራና በቀላሉ ወድቀው የማይሰበሩ፤ ቢሰበሩም በጽናት ታግለው የሚያሸንፉ ግለሰቦችና ቤተሰቦች ቢጐድሉትም፤ አዝናኝና እውቀት ከማቀበልና መረጃ ከመስጠት ይልቅ ልብ-ሰቃይ ታሪክ በመፍጠር ግን የታወቀና የተደነቀ ነው፤ መቼ መጥተው ጉዳቸውን ባየነው የሚያስብል፡፡የአስናቀ ጉዳይ ግን ከወዲሁ ቢታሰብበት አይከፋም፡፡እነዚህ ጥቂት ምሳሌዎች ናቸው፤ በጥንቃቄ የተቀረፁ ደጋግም ሆነ ክፉ ገፀ-ባህርያት በአንባብያን ላይ የሚያጠሉት ጥላ ቀላል አይደለም፤ የጀርመናዊውን ጐቴ (1749-1832) "The sorrows of young werther" የተባለውን መጽሐፍ ያነበቡ ብዙ ወጣቶች ራሳቸውን ገድለዋል፡፡ በዚህ ስለፍቅር በሚተርከው ልቦለድ ላይ ያለው ገፀባህርይ በታሪኩ መጠናቀቂያ ላይ ራሱን ያጠፋል፤ ይህን ያነበቡና የወጣቱ ውሳኔ ልክ ነው ያሉ- ጥቂት አንባብያን እጃቸውን በእጃቸው በልተዋል፡፡…መስፍን ሃብቱ የሚባል አንድ ኢትዮጵያዊም ነበር- በ1960ዎቹ መጀመሪያ በባዕድ ሀገር ራሱን ያጠፋ፤ ይህ በአሜሪካ አገር የተማሪዎችን ንቅናቄ በመምራትና ፓርቲ በማደራጀት የሚታወቅ ወጣት፤ ራሱን ለማጥፋት ያበቃውን ‹ፀፀት› ለጊዜው እንተወውና ከመሞቱ በፊት ግን አንድ ፊልም እያየ ነበር- ፊልሙ ስለ አንድ ታዋቂ የደች ሰዓሊ (ቫንጐህ ነው ሰውየው) ይተርካል፣ ፊልሙ ሊጠናቀቅ ሲል ይህ ታላቅ ሰዓሊ ራሱን ያጠፋል፤ መስፍን ይህንን ፊልም አየ፤ ቤቱ ገባ፤ በሰራው ፖለቲካዊ ስህተት እጅጉን ተፀፅቶ፤ በጓደኞቹ ዘንድ በደረሰበት መገለል ክፉኛ ተጐድቶ ነበርና፤ ለመጽናናት ብሎ ከከፈተው ፊልም አንዳች ነገር ወሰደ፤ መፍትሄ አገኘ፤ እንደ ፊልሙ ባለታሪክ- በሰው ሃገር ራሱን ገደለ፡፡እንደ ኢትዮጵያ ባሉ-ድህነት ቀፍድዶ በያዛቸው ሀገራት ይቅርና በሰለጠኑት ዓለማትም ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማዎች ሳናውቀው በልባችን ውስጥ ከባድ ማኅተም ያሳርፋሉ፤ በአመለካከታችን ላይ ተፅዕኖ ያሳድራሉ፤ የተንኮልን ተክል ወይም የደግነትን አበባ ይዘራሉ፤ እቤታችን አስገብተን በፈቃደኝነት እንማርላቸዋለን ለዚህም ነው ከልቦለድም ከቴአትርም በላይ ተከታታይ ድራማዎች አስተውሎትን የሚጠይቁት፡፡ ትልቁም ትንሹም እኩል የሚከታተለው ነውና፤ ምሁሩም መሐይሙም በአንድ የመዝናኛ ገበታ እንዲታደሙ የሚያደርግ ነውና!…ከመርፈዱ በፊት መንቃት ያስፈልጋል ለማለት ነው ይሄ ሁሉ፤ አስበውበት ከሆነ እሰየው፤ ካላሰቡበት ደግሞ እንዳይዘናጉ ለማስታወስ ነው……‹አርአያ› እንዳናጣ፣ ከራሳችን እንዳንጣላ፣ ራሳችንን እንዳናጠፋ፣ ሰብዕናችንን እንዳናቆሽሽና በተሳሳተ መንገድ እንዳንማርና እንዳናስተምር ለእናንተም፣ ለእኔም ለመሰሎቻችንም የተፃፈ ማስታወሻ ነው - ይሄ፡፡ከአክብሮት ጋር፡፡
Published on August 24, 2013 06:14
እንዳለጌታ ከበደ's Blog
- እንዳለጌታ ከበደ's profile
- 42 followers
እንዳለጌታ ከበደ isn't a Goodreads Author
(yet),
but they
do have a blog,
so here are some recent posts imported from
their feed.

